ሁለት የእስራኤል ሚኒስትሮች የጥምር መንግስቱን እናፈርሳለን ሲሉ ዛቱ
ሚኒስትሮቹ ኔታንያሁ በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የቀረበውን የተኩስ አቁም እቅድ ከተቀበሉት ነው ስልጣን እንለቃለን ያሉት
ሃማስ በበኩሉ በባይደን የቀረበውን የተኩስ አቁም ሃሳብ በበጎ እንደሚመለከተው ገልጿል
ሁለት ቀኝ ዘመም የእስራኤል ሚኒስትሮች ስልጣን ለቀው የጥምር መንግስቱን እንደሚያፈርሱ ዛቱ።
የፋይናንስ ሚኒስትሩ ቤዛለል ስሞትሪች እና የብሄራዊ ደህንነት ሚኒስትሩ ኢታማር ቤን ግቪር ናቸው የጥምር መንግስቱን እንደሚያፈርሱ የተናገሩት።
ሁለቱ ሚኒስትሮች ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ያቀረቡትን የተኩስ አቁም እቅድ የሚቀበሉት ከሆነ ስልጣን እንለቃለን ብለዋል።
ሚኒስትሮቹ ሃማስ ሙሉ በሙሉ ሳይደመሰስ የሚፈጸም የትኛውንም ስምምነት እንቃወማለን ማለታቸውንም ቢቢሲ ዘግቧል።
በፓርላማው 24 መቀመጫዎች ያሉት የሽ አቲድ ፓርቲ መሪው ያኢር ላፒድ ግን ኔታንያሁ የተኩስ አቁም ስምምነቱን ለማድረግ ቢፈቅዱ እንኳን ድጋፍ እንደሚሰጧቸው አስታውቀዋል።
የእስራኤል የጦር ካቢኔ አባሉ ቤኒ ጋንዝ፥ ኔታንያሁ የድህረ ጋዛ ጦርነትን በተመለከተ ግልፅ እቅድ ካላቀረቡ ስልጣን እንደሚለቁ መናገራቸው ይታወሳል።
የጋዛው ጦርነት የጥምር መንግስታቸውን ህልውና አደጋ ውስጥ የጣለባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በበኩላቸው የሃማስ ወታደራዊ እና አስተዳደራዊ አቅም እስካልፈራረሰና ሁሉም ታጋቾች እስካልተለቀቁ ድረስ ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት እንደማይደረስ ደጋግመው ገልጸዋል።
በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ እስራኤላውያን በቴል አቪቭ ባደረጉት ሰልፍ ኔታንያሁ በአሜሪካ የቀረበውን የተኩስ አቁም እቅድ እንዲቀበሉ ጠይቀዋል።
ሰልፈኞቹ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን እንዲለቁ የጠየቁ ሲሆን፥ የኔታንያሁ የተኩስ አቁም እቅዱን አለመቀበል የበርካታ ታጋቾችን ህይወት ይበልጥ አደጋ ላይ ይጥላል ሲሉም ተደምጠዋል።
የፍልስጤሙ ሃማስ በባይደን የቀረበውንና በሶስት ምዕራፎች የሚተገበረውን የተኩስ አቅም እቅድ በበጎ እንደሚመለከተው አስታውቋል።
የእስራኤል ጦር በስድስት ሳምንታት ውስጥ በርካታ ፍልስጤማውያን ከሚኖሩባቸው አካባቢዎች እንዲወጡ፤ በሃማስ የታገቱ ሰዎች እንዲለቀቁና ቋሚ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ የሚጠይቀው የአሜሪካ የተኩስ አቁም እቅድ ግን በእስራኤል በኩል እስካሁን ተቀባይነት ስለማግኘቱ አልተገለጸም።
የግብጽ፣ ኳታር እና አሜሪካ አደራዳሪዎች በትናንትናው እለት በጋራ ባወጡት መግለጫ እስራኤልና ሃማስ ባይደን ያቀረቡትን እቅድ እንዲያጠናቅቁ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።