በጋዛው ጦርነት ከፍተኛ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች መካከል አንዱ የሆኑት ዩአቭ ጋላንት ከኔታንያሁ ጋር ለወራት አለመግባባት ውስጥ ነበሩ
ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ታዋቂው የመከላከያ ሚንስትራቸው ዮአቭ ጋላንትን ከሀላፊነት ማንሳታቸው ተሰምቷል፡፡
እስራኤል በተለያዩ የጦርነት ግንባሮች ከባድ ውግያ እያደረገች በምትገኝበት ወቅት የተወሰነው ይህ ድንገተኛ ውሳኔ ተቃውሞን አስነስቷል፡፡
ኔታንያሁ እና ጋላንት በጋዛ ጦርነት ምክንያት በተደጋጋሚ ከፍተኛ የሀሳብ ልዩነት እና አለመግባባት ውስጥ እንደቆዩ የተለያዩ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሀን ዘግበዋል፡፡
ጠቅላይ ሚንስትሩ የአለም ትኩረት በአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ላይ በነበረበት ወቅት ውሳኔውን ካሳለፉ በኋላ ጋላንት “የአመራር ክፍተት እና የእምነት ችግር የነበረባቸው ሰው ነበሩ” ብለዋል፡፡
ኔታንያሁ በንግግራቸው “በጦርነት መካከል ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በጠቅላይ ሚኒስትሩ እና በመከላከያ ሚኒስትሩ መካከል ሙሉ እምነት ያስፈልጋል፤ ምንም እንኳን በዘመቻው የመጀመሪያዎቹ ወራት በጠንካራ መተማመን ፍሬያማ ሥራ አብረን መስራት ብንችልም እንደአለመታደል ሆኖ በቅርብ ወራት ይህ መተማመን በእኔ እና በመከላከያ ሚኒስትሩ መካከል ንፋስ ገብቶታል” ብለዋል፡፡
እስራኤል አዲስ ወታደር ለመመልመል ፈተና እንደገጠማት ተገለጸ
በጦርነቱ የመጀመሪያዎቹ ቀናት የእስራኤል ከፍተኛ አመራሮች ለሀማስ ኦክቶበር 7 ጥቃት ምላሽ ለመስጠት ወጥ የሆነ አንድነትን አሳይተው ነበር፡፡
ነገር ግን የጦርነቱ መራዘም እና ሊባኖስን ጨምሮ ወደሌሎች የቀጠናው ሀገራት እየተስፋፋ መምጣቱ በአመራሮች መካከል በቁልፍ የፖሊሲ ጉዳዮች ላይ ልዩነቶች እንዲበረክቱ ምክንያት ሆኗል ።
ኔታንያሁ በሃማስ ላይ ወታደራዊ ጫና እንዲቀጥል “ፍጹም አሸናፊነትን” መቀዳጀት እንደሚፈልጉ ሲገልጹ፤ ጋላንት በበኩላቸው ጦሩ ለፖለቲካዊ መፍትሄዎች መንገዱን መጥረጉን በመናገር ጦርነቱ እንዲያቆም እና ድርድር እንዲቀጥል ሀሳባቸውን አንጸባርቀዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ጋላንት ለጥቅምት ሰባቱ ጥቃት ተጠያቂ በሁኑ የፖለቲካ እና ወታደራዊ አመራሮች ላይ ገለልተኛ ምርመራ እንዲደረግም በተደጋጋሚ ሲጠይቁ ተሰምተዋል፡፡
በርካታ የታጋች ቤተሰቦች እና የመንግስት ተቃዋሚዎች ኔታንያሁ የስልጣን ዘመናቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ ጦርነቱን ለማራዘም እና ከተኩስ አቁም ስምመነትን ማፍረስ መፍትሄ አድርገው ይዘውታል ሲሉ ይከሳሉ፡፡
የዮአቭ ጋላንትን ከስልጣን መሰናበት ተከትሎ በማዕከላዊ ቴልአቪቭ እና በሌሎች አካባቢዎች ህዝባዊ ተቃውሞ ተቀስቅሷል፡፡
የተቀናቃኝ ፓርቲ መሪው ያየር ላፒድ በዚህ ወቅት የመከላከያ ሚንስትርን ከስራ ማሰናበት “እብደት ነው” ሲሉ ቅሬታቸውን በኤክስ (ትዊተር) ገጻቸው ላይ አስፍረዋል፡፡
በቴልአቪቭ አደባባዮች የወጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች ዋና ዋና መንገዶችን በመዝጋት ወደ ጠቅላይ ሚንስትሩ መኖርያ ቤት በማቅናት ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡
በርካታ የኔታንያሁ ተቃዋሚዎች እና የፖለቲካ ሀይሎች ጠቅላይ ሚንስትሩ ጦርነቱን ስለማቆም የሚጠይቁ ከፍተኛ አመራርን ማሰናበታቸው በጋዛ እና ሊባኖስ ሀገሪቱን የማትወጣው ቀውስ ውስጥ ለመክተት መወሰናቸውን ያሳያል ብለዋል፡፡