እስራኤል ወታደሮቿ እረፍት እንዳይጠይቁ አገደች
ኢራን በሶሪያ ለተገደሉባት ጀነራሎች የአጻፋ እርምጃ እወስዳለሁ ማለቷን ተከትሎ ቴል አቪቭ የደህንነት ስርአቷን ማጠናከሯ ተገልጿል
ቴህራን በረመዳን ወር የመጨረሻ አርብ ጥቃት ልትፈጽም ትችላለች የሚለው ስጋት አይሏል ተብሏል
የእስራኤል ጦር ሁሉም የሀገሪቱ ወታደሮች እረፍት እንዳይጠይቁ ጊዜያዊ ክልከላ አወጣ።
ጦሩ ባወጣው መግለጫ “ወቅታዊ ሁኔታዎችን በመገምገም ሁሉም በግዳጅ ላይ ያለ ወታደር እረፍት እንዳይወጣ ተወስኗል፤ እንዳስፈላጊነቱም አዳዲስ ስምሪቶች ሊኖሩ ይችላሉ” ብሏል።
ክልከላው የተላለፈው በምን ምክንያት እንደሆነ ጦሩ በመግለጫው ባያነሳም እስራኤል ከኢራን ጋር የገባችበት ውጥረት ዋነኛው መንስኤ መሆኑን ሬውተርስ ዘግቧል።
የኢራን ሁለት ጀነራሎች እና አምስት ወታደራዊ አማካሪዎች በሶሪያ መዲና ደማስቆ በአየር ጥቃት ከተገደሉ በኋላ ቴህራን የአጻፋ እርምጃ እንደምትወስድ መዛቷ ይታወሳል።
እስራኤል እስካሁን ጥቃቱን መፈጸሟን አልገለጸችም፤ የቴህራንን ወቀሳም አላጣጣለችም።
የኢራኑ ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲ ግን ጥቃቱን የፈጸመችው እስራኤል ላይ ፈጣን አጻፋዊ እርምጃ እንወስዳለን ሲሉ መዛታቸው ይታወሳል።
እስራኤል በኢራን ከሚደገፉት የፍልስጤሙ ሀማስ፣ የሊባኖሱ ሄዝቦላህ እና የየመኑ ሃውቲ ጋር ጦርነት ውስጥ ከገባች ከነገ በስቲያ ስድስት ወር ትደፍናለች።
ቴህራን እስካሁን በጋዛው ጦርነት በቀጥታ ባትሳተፍም በምታስታጥቃቸው ሃይሎች ፍላጎቷን እያስፈጸመች መሆኑ ይታመናል።
ባለፈው ሰኞ በደማስቆ ለተፈጸመው ጥቃትም በአጋሮቿ በኩል የአጻፋ እርምጃ ልትወስድ ትችላል በሚል ቴል አቪቭ የደህንነት ስርአቷን ማጠናከሯ ተገልጿል።
በቴል አቪቭ እና ሌሌች ከተሞች የአቅጣጫ መጠቆሚያ (ጂፒኤስ) አገልግሎት መታወኩን ነዋሪዎች ለሬውተርስ ተናግረዋል። ይህም በጂፒኤስ በሚታዘዙ ሚሳኤሎች የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለመቀነስ ያለመ ነው ተብሏል።
ቴህራን በረመዳን ወር የመጨረሻ አርብ ጥቃት ልትፈጽም ትችላለች የሚለው ስጋት ማየሉም እስራኤል ጦሯ በተጠንቀቅ እንዲጠባበቅ እንድታዝ ማድረጉ ተመላክቷል።