203 ትምህርት ቤቶችና 80 የመንግስት መስሪያ ቤት ህንጻችም በአየር ድብደባው ወድመዋል
ከ23 ቀናት በፊት ለፍልስጤም ነጻነት እታገላለሁ የሚለው ሃማስ በእስራኤል ላይ ያልታሰበ ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎ በአካባቢው ጦርነት ተቀስቅሷል።
የሃምስን ድንገተኛና ያልተጠበቀ ጥቃትን ተከትሎ ጋዛን በአየር ስትደበድብ የከረመችው እስራኤል በርካታ መሰረተ ልማቶችን እና ተቋማትን አውድማለች።
በዚህም እስራኤል ባለፉት 23 ቀናት ያለማቋረጥ በጋዛ ላይ በፈተጸመችው የአየር ድብደባ 47 መስጊዶች እና 7 ቤተ ክርስቲያኖች መውደማቸውን የጋዛ ባለስልጣናት አስታውቃዋል።
በተጨማሪም 203 ትምህርት ቤቶችና 80 የመንግስት መስሪያ ቤት ህንጻችም በእርሳኤል የአየር ድብደባ መውደማቸውን ነው ባለስልጣናቱ የገለጹት።
የጋዛ ሚዲያ ቢሮ ዳይሬክተር ሳላማ ማሩፍ እንደተናገሩት፤ በእስራኤል የአየር ድብደባ በሺዎች የሚቆጠሩ መኖሪያ ቤቶች መውደማቸውን ገልጸዋል።
በዚህም በውስጣቸው 220 ሺህ መኖሪያ ቤቶችን የያዙ 32 ሺህ ህንጻች ሙሉ በሙሉ ወድመዋል ብለዋል።
የእስራኤል ጦር በጋዛ የሚገኝና ከ1 ሺህ 500 በላይ ፍሊስጤማውያንን ያጠለለችወን የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የባህል ማእከል እና ትምህርት ቤትን እንደሚመታ አስጠንቅቋል።
እስራኤል እየወሰደችው ባለው የአጻፋ እርምጃም ከ8 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን ህይወት መቀጠፉን የፍልስጤም የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
ከሞቱ ሰዎች መካከልም ከ3 ሺህ በላይ ህጻናት፤ 2 ሺህ ደግሞ ሴቶች ናቸው ሲሆኑ፤ ከ20 ሺህ በላይ ፍሊስጤማውያን ቆስለዋል።