እስራኤል በጋዛ “የዘር ጭፍጨፋ” እየፈጸመች ነው - የሳኡዲ ልኡል አልጋወራሽ
ልኡል አልጋወራሽ መሀመድ ቢን ሳልማን እስራኤል በሊባኖስ እና ኢራን የምትፈጽመውን ጥቃትም ኮንነዋል
የአረብና ሙስሊም ሀገራት መሪዎች በጋዛና ሊባኖስ ወቅታዊ ጉዳይ በሪያድ ተወያይተዋል
የሳኡዲ ልኡል አልጋወራሽ መሀመድ ቢን ሳልማን እስራኤል በጋዛ “የዘር ጭፍጨፋ” እየፈጸመች ነው ሲሉ አጥብቀው ተቃወሙ።
ልኡል አልጋወራሹ የጋዛ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ጠንከር ባለ ቃል ቴል አቪቭን ያወገዙት የሙስሊምና አረብ ሀገራት መሪዎች ጉባኤ በሪያድ ሲጀመር ባደረጉት ንግግር ነው።
እስራኤል በኢራን እና ሊባኖስ እየፈጸመች የምትገኘውን ጥቃትም የሳኡዲው ልኡል አልጋወራሽ ኮንነዋል።
የሪያድ እና ቴህራን ግንኙነት እየተሻሻለ መምጣቱን በሚያሳይ መልኩም እስራኤል በኢራን መሬት ላይ ጥቃት እንዳትፈጽም አሳስበዋል።
ሌሎች የጉባኤው ተሳታፊ ሀገራት መሪዎችም እስራኤል ከዌስትባንክ እና ጋዛ ሙሉ በሙሉ እንድትወጣ ጥሪ ማቅረባቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
በተያያዘ የሳኡዲ አረቢያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ልኡል ፈይሰል ቢን ፋርሃን አል ሳውድ “የእስራኤልን የጋዛ ወረራ ማስቆም ያልተቻለው በአለማቀፉ ማህበረሰብ ድክመት ነው፤ እስራኤል ህዝብ እያስራበች ትገኛለች” ሲሉ ተናግረዋል።
የሙስሊምና አረብ ሀገራት መሪዎች በሪያዱ ጉባኤ እስራኤል በመንግስታቱ ድርጅት ሰራተኞችና ተቋማት ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት አውግዘዋል።
የእስራኤል ፓርላማ (ክኔሴት) ባለፈው ወር በመንግስታቱ ድርጅት የፍልስጤማውያን የስደተኞች ኤጀንሲን በእስራኤል፣ ዌስትባንክ እና ምስራቅ እየሩሳሌም እንዳይንቀሳቀስ የሚያግድ ህግ ማጽደቁ ይታወሳል።
አሜሪካ እና ብሪታንያን ጨምሮ የኤጀንሲው መታገድ የጋዛን ሰብአዊ ቀውስ ያባብሳል በሚል ስጋታቸውን ቢገልጹም የኔታንያሁ አስተዳደር ላይ ጫና ማሳደር አልቻሉም።
የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ሪፐብሊካኑን ዶናልድ ትራምፕ ለዳግም ድል ማብቃቱን ተከትሎ "ሶስት ጊዜ ለትራምፕ ደውያለሁ" ያሉት ኔታንያሁ በሰሜናዊ ጋዛም ሆነ በሊባኖስ ጥቃታቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል።
የሪያዱ ጉባኤም በዋይትሃውስ ቆይታቸው የሙስሊሙን አለም ያስቆጡ ውሳኔዎችን ያሳለፉት ዶናልድ ትራምፕ ድጋሚ በተመረጡበት ሰሞን ነው የተካሄደው።
በርግጥ ትራምፕ እየሩሳሌም የእስራኤል መዲና መሆኗን አውጀው የአሜሪካን ኤምባሲ ከቴል አቪቭ ወደ እየሩሳሌም ማዛወራቸውና በሃይል የተያዙ የጎላን ኮረብታዎች የእስራኤል ግዛት አካል ማድረጋቸው በአረብና ሙስሊም ሀገራት ትችት ቢያስነሳባቸውም ከበርካታ ሀገራት ጋር ወዳጅነትን መስርተዋል።
ትራምፕ የባህረ ሰላጤው ሀገራት በ2020 ከእስራኤል ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን እንዲያድሱ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።
ሳኡዲም ትራምፕ ምንም እንኳን በመካከለኛው ምስራቅ ጉዳይ አወዛጋቢ ውሳኔዎችን ቢያሳልፍም ከዴሞክራቱ ጆ ባይደን ይልቅ የትራምፕን ዳግም መመረጥ በበጎው ትመለከተዋለች ይላል የቢቢሲ ዘገባ።
ሪያድ በዋሽንግተን ሸምጋይነት ከቴል አቪቭ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለመጀመር የሚደረገው ጥረት እንዲሳካም ትራምፕ ከባይደን በተሻለ የጋዛውን ጦርነት በፍጥነት ሊያስቆመው እንደሚችል ትጠብቃለች።