እስራኤል ጋዛን በመክበብ ጥቃት አድራሾችን ለመግደል መጠነ ሰፊ ጦር በደቡብ እስራኤል አሰማርታለች
የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር በዛሬው እለት የሀማስ መቀመጫ የሆነችው የጋዛ ግዛት "ሙሉ በሙሉ" እንድትከበብ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።
የእስራኤል- ሀማስ ግጭት ዛሬ ሶስተኛ ቀኑን አስቆጥሯል።
ሚኒስትሩ እንደገለጹት የእስራኤል ጦር የሀማስ ታጣቂዎች ዘልቀው የገቡባቸውን የእስራኤል መንደሮች መልሶ ተቆጣጥሯል።
ሚኒስትሩ ዮአብ ጋላንት፣ ጋዛ መብራት፣ ምግብ፣ ውሃ እና ነዳጅ የምታገኝባቸው መስመሮች ይዘጋሉ ብለዋል።
"ጋዛ ሙሉ በሙሉ እንድትከበብ ትዕዛዝ ሰጥቻለሁ" ብለዋል ሚኒስትሩ።
"እየተዋጋን ያለነው ከአረመኔዎች ጋር ነው፤ አጸፋው በዚሁ ልክ ነው" ሲሉ ሚኒስትሩ አክለዋል።
ሀማስ በ50 አመታት ውስጥ በእስራኤል ላይ ባደረሰው "ከባድ እና ያልተጠበቀ" ጥቃት እስካሁን የሞቱ እስራኤላውያን ቁጥር 700 መድረሱን የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ሪር አድሚን ዳንኤል ሀጋሪ አስታውቀዋል።
ሀማስ ከጋዛ ሮኬት በማዝነብ እና በታጣቂዎቹ በመታገዝ ነበር ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግለትን የእስራኤል ድንበር ጥሶ መግባት የቻለው።
ይህን ጥቃት ተከትሎ እስራኤል በወሰደችው የአጸፋ እርምጃ በጋዛ በመቶዎች ተገድለዋል፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ ተሰደዋል።
እስራአል እንደ ሀገር ከተመሰረተችበት እንደፈረንጆቹ ከ1948 ወዲህ በዚህ ልክ ድንበሯ ተሰብሮ ጥቃት አልደረሰባትም።
በዚህ ክፉኛ የተናደደችው እስራኤል ጋዛን በመክበብ ጥቃት አድራሾችን ለመግደል መጠነ ሰፊ ጦር በደቡብ እስራኤል አሰማርታለች።
አሜሪካን ጨምሮ ምዕራባውያን ሀገራት ከእስራኤል ጎን እንደሚቆሙ በመግለጽ አጋርነታቸውን አሳይተዋል።
ሀማስ አሜሪካ የጦር መርከብ በመላክ "በፍልስጤም ህዝብ ላይ በሚደረገው ወረራ እየተሳተፈች" ነው የሚል ክስ አቅርቧል።