የእስራኤል ጦር ጋዛን ከግብጽ ጋር የሚያገናኘውን ወሳኝ ማቋረጫ ተቆጣጠረ
ሀማስ፣ እስራኤል ጥቃት በመክፈት በካይሮ እየተካሄደ ባለው የተኩስ አቁም ድርድር ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረች ነው ሲል ከሷል
የእስራኤል ጦር በጋዛ እና ግብጽ መካከል ያለውን ወሳኝ ማቋረጫ በመቆጣጠር ወደ ራፋ ከተማ እየገሰገሰ ነው ተብሏል
የእስራኤል ጦር ጋዛን ከግብጽ ጋር የሚያገናኘውን ወሳኝ ማቋረጫ ተቆጣጠረ።
አለምአቀፍ አደራዳሪዎች፣ እስራኤል እና ሀማስ ተኩስ ለማቆም እንዲስማሙ ጥረት እያደረጉ ባለበት ወቅት የእስራኤል ጦር በጋዛ እና ግብጽ መካከል ያለውን ወሳኝ ማቋረጫ በመቆጣጠር ወደ ራፋ ከተማ እየገሰገሰ ነው ተብሏል።
ሀማስ፣ እስራኤል ጥቃት በመክፈት በካይሮ እየተካሄደ ባለው የተኩስ አቁም ድርድር ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረች ነው ሲል ከሷል።
አለምአቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ወደ ደቡባዊ ጋዛ የሚያደርሱ ሁለት ማቋረጫዎችን ማለት ኬረም ሻሎምን እና ራፋን መዝጋት የእርዳታ ክምችት እየተመናመነ ያለባት ጋዛ ምንም አይነት እርዳታ ከውጭ እንዳታገኝ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
የእስራኤል ጦር ራዲዮ፣ የእስራኤል ጦር በፍልስጤም በኩል ያለውን የራፋ ማቋረጫ ዛሬ ጠዋት መቆጣጠሩን ያስታወቀ ሲሆን ጦሩ የለቀቀው ቪዲዮ ደግሞ ታንኮቹን ሲያንቀሳቅሳ ያሳያል።
እስራኤል የራፋ ከተማን ከማጥቃት እንድትቆጠብ አለምአቀፍ ጫና ቢደረግባትም፣ ሀማስን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት ያለመችው እስራኤል የሀማስ የመጨረሻ ምሽግ የሚገኝባትን ራፋን ማጥቃት ጀምራለች።
ሀማስ፣ ኳታር እና ግብጽ ያቀረቡትን በሶስት ምዕራፍ የተከፋፈለ የተኩስ አቁም ስምምነት እቅድ እንደተቀበለው አሳውቋል።ዠ
ይህ እቅድ ሀማስ ታጋቾችን በመልቀቅ፣ በምላሹ እስራኤል ፍልስጤማውያን እስረኞችን እንድትፈታ መንገድ መክፈት፣ ዘላቂ ተኩስ አቁም ማድረግ እና የእስራኤል ጦር ሙሉ በሙሉ ከጋዛ እንዲወጣ ማድረግ የሚሉ ነጦቦችን አካቷል።
ነገርግን የተኩስ አቁም ስምምነት እቅዱ ትክክለኛ ፍላጎቷን ያላገናዘበ መሆኑን የገለጸችው እስራኤል አልተቀበለችውም።
ከኳታር እና ግብጽ ጋር በመሆን የአደራዳሪነት ሚና ስትጫወት የነበረችው አሜሪካ፣ የሀማስን ምላሽ እያጠናችው እንደምትገኝ እና በጉዳዩ ላይ ከመካከለኛው ምስራቅ አጋሮቿ ጋር እንደምትመክርበት ገልጻለች።