የእስራኤል ካቢኔ በደህንነት ስጋት ምክንያት የስብሰባ ቦታውን እየቀያረ ነው ተባለ
ሂዝቦላህ ጥቃት ሊያደርስ ይችላል በሚል የእስራኤል ካቢኔ ቋሚ መሰብሰቢያ ቦታውን ቀይሯል
ሂዝቦላህ ከዚህ በሰነዘራቸው ሁለት ጥቃት ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ መኖሪያ ቤትን ማጥቃቱ ይታወሳል
የእስራኤል ካቢኔ በደህንነት ስጋት ምክንያት የስብሰባ ቦታውን እየቀያረ ነው ተባለ፡፡
ከአንድ ዓመት በፊት የፍልስጤሙ ሐማስ በእስራኤል ላይ ልተጠበቀ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ የተጀመረው ጦርነት አድማሱን እያሰፋ ይገኛል፡፡
ከአንድ ወር በፊት በሊባኖሱ ሂዝቦላህ እና እስራኤል ጦር መካከል ይፋዊ ጦርነት የተጀመረ ሲሆን የእስራኤል ጦር ወደ ደቡባዊ ሊባኖስ ገብቶ ከሂዝቦላህ ተዋጊዎች ጋር እየተዋጋ ይገኛል፡፡
ሂዝቦላህ ወደ እስራኤል ከተሞች የአየር ላይ ጥቃቶችን በማድረስ ላይ ሲሆን የጠቅላይ ሚኒስትሮ መኖሪያ ቤት፣ የሀገሪቱ የስለላ ተቋም ሞሳድ እና ሌሎች ወታደራዊ ተቋማት ዋነኛ ኢላማ ሆነዋል፡፡
ይህን ተከትሎ በጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የሚመራው የሀገሪቱ ካቢኔ መደበኛ ስብሰባ ቦታ ተቀይሯል ተብሏል፡፡
እንደ ዘ ታይምስ ኦፍ እስራኤል ዘገባ ከሆነ የሀገሪቱ ካቢኔ ስብሰባ ቦታ የተቀየረው በደህንነት ስጋት ምክንያት ነው፡፡
ከዚህ በፊት የእስራኤል ካቢኔ ስብሰባ በሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ውስጥ ይደረግ የነበረ ሲሆን ከዛሬ ጀምሮ ግን በደህንነት ስጋት ምክንያት የስብሰባ ቦታው ተቀይሯል፡፡
ሂዝቦላህ በሰሜናዊ እስራኤል የ14 መኖሪያ መንደር ነዋሪዎች ቤታቸውን እንዲለቁ አስጠነቀቀ
የካቢኔ ስብሰባው ከዛሬ ጀምሮ በባንድ ቦታ ሳይሆን በተለያዩ ቦታዎች ላይ ይካሄዳል የተባለ ሲሆን ስብሰባው በቋሚ ቦታ እንዳይካሄድ ተወስኗል፡፡
ሂዝቦላህ በትናንትናው ዕለት በሁለቱ ድንበር አቅራቢያ ባሉ 14 መኖሪያ መንደሮች ውስጥ የሚኖሩ እስራኤላዊያን ቤታቸውን ባስቸኳይ እንዲለቁ ማስጠንቀቁ ይታወሳል፡፡
ሂዝቦላህ በሰሜናዊ እስራኤል የሚኖሩ እስራኤላዊያን መኖሪያ ቤታቸውን እንዲለቁ ያስጠነቀቀው የሀገሪቱ ጦር ነዋሪዎች ባሉባቸው አካባቢዎች ሰፍሯል በሚል ነው፡፡
ነዋሪዎች ማስጠንቀቂያ ችላ ብለው ለሚደርስባቸው ጥቃት ሀላፊነቱን እንደማይወስድም ሂዝቦላህ አስታውቋል፡፡