ፕሬዝደንት ሉላ በእስራኤል "የማይፈለጉ ሰው" ተብለው ተፈረጁ
የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በእስራኤል የብራዚል አምባሳደር የሆኑትን ፌደሪኮ ማየርን ለማስጠንቀቅ ጠርቷል
እስራኤል ፕሬዝደንት ሉላን በእስራኤል "የማይፈለጉ ሰው" ብላ የፈረጀችው የጋዛን ጦርነት ሂትለር ከፈጸመው የዘር ማጥፋት ጋር በማነጻጸራቸው ነ
ፕሬዝደንት ሉላ በእስራኤል "የማይፈለጉ ሰው" ተብለው ተፈረጁ።
እስራኤል ፕሬዝደንት ሉላን በእስራኤል "የማይፈለጉ ሰው" ብላ የፈረጀችው የጋዛን ጦርነት ሂትለር ከፈጸመው የዘር ማጥፋት ጋር በማነጻጸራቸው ነው።
የብራዚሉ ፕሬዝዳንት ሉላ ዳ ሲልቫ በሰጡት እስራኤልን የተመለከተ አስተያየት ምክንያት በእስራኤል "የማይፈለጉ ሰው" መሆናቸውን የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ፕሬዝደንት ሉላ ለ37ኛው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ተጋብዘው በተገኙበት ወቅት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እስራኤል በጋዛ የምታካሂደውን ጦርነት በሁለተኛው የአለም ጦርነት ናዚ ከፈጸመው የዘር ማጥፋት ጋር ማነጻጸራቸው እስራኤልን ክፉኛ አስቆጥቷል።
ፕሬዝደንቱ "በጋዛ ሰርጥ በፍልስጤማውያን ላይ እየተከሰተ ያለው ከሌሎች ታሪካዊ ሁነቶች ጋር የማይስተካከል ነው። በርግጥ እንዲህ አይነቱ ተግባር ሂትለር ጀዊሾችን ለመግደል የወሰነ ጋዜ ተከስቷል" ብለዋል።
በዚህ ንግግር የተቆጣው የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በእስራኤል የብራዚል አምባሳደር የሆኑትን ፌደሪኮ ማየርን ለማስጠንቀቅ መጥሯቱን የእስራኤሉ አይ24 ኒውስ ዘግቧል።
የእስራኤል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ "አንረሳምም፤ ይቅርም አንል። ይህ ከባድ የጸረ-ጽዮናውያን ጥቃት ነው። በእኔ ስም እና በእራኤል መንግስት ስም ፕሬዜዳንት ሉላ አስተያየታቸውን እስኪያነሱ ድረስ በእስራኤል የማይፈለጉ ሰው ናቸው" ብለዋል።
"የእስራኤልን ፍትሃዊ ጦርነት እና ሂትለር የፈጸመውን ግፍ ማነጻጸር ነውር፣ አስቀያሚ እና ጸረ-ጽዮናዊነት ነው"ሲሉም ካቲዝ ተናግረዋል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስቴር ቤንያሚን ኔታንያሁም የፕሬዝደንት ሉላን አስተያየት "ደስ የማይል እና ስህተት"የሆነ ሲሉ ገልጸውታል።
በብራዚል የሚገኘው የእስራኤላውያን ኮንፌደሬሽን የፕሬዝደንት ሉላ አስተያየት "እውነታውን የሚያዛባ" እና የዘር ማጥፋት ሰለባዎችን እና ቤተሰቦቻቸውን ትውስታ የሚጎዳ በመሆኑ እንደሚቃወመው ገልጸዋል።
ኮንፌደሬሽኑ አክሎም የሉላ መንግስት በእስራኤል እና ሀማስ ጦርነት ዙሪያ "ጫፍ የወጣ እና ሚዛናዋ ያልሆነ" አቋም ይዟል ሲሉ ከሰዋል።
ፕሬዝደንት ሉላ ይህን አስተያየት ከመስጠታቸው ቀደም ብለው ለፍስጤማውያን የሰብአዊ እርዳታ ለሚያደርሰው የተመድ ኤጀንሲ ድጋፍ መቋረጡን አውግዘው ነበር።
ፕሬዝደንቱ "ጦርነቱ በወታደሮች እና በወታደሮች መካከል የሚደረግ አይደለም፤ ከፍተኛ ዝግጅት ባደረገ ወታደር እና በሴቶች እና በህጻናት መካከል እየተደረገ ያለ ጦርነት "ብለዋል።
እስራኤል በጋዛ እያካሄደች ባለው መጠነ ሰፋ ጦርነት እስካሁን የተገደሉ ፍልስጤማውያን ቁጥር ከ29ሺ ማለፉ ተገልጿል።