የአባ ፍራንሲስ የጤና ሁኔታ በአስጊ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ቫቲካን አስታወቀች
የአባ ፍራንሲስ የጤና ሁኔታ ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ መባባሱን ቫቲካን ትናንት አስታውቃለች

የሮማው ጳጳስ አባ ፍራሲስ በሳምባ ምች ተጠቅተው ሆስፒታል መግባታቸው ይታወቃል
የሮማ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳስ አባ ፍራንሲስ የጤና ሁኔታ በአስጊ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ቫቲካን አስታወቀች።
ቫቲካን ትናንት የሊቀ ጳጳሱን የጤና ሁኔታ አስመልታ ባወጣች መግለጫ፤ የአባ ፍራንሲስ የጤና ሁኔታ ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ መባባሱን አስታውቃለች።
የሮማው ጳጳስ ፍራንሲስ በተመንፈሻ አካላቸው ላይ ያጋጠማቸውን ህመም ለመታካም ሆስፒታል ከገቡ 10ኛ ቀናቸውን ማስቆጠራቸውን ቫቲካን የእሳቸውን ሁኔታ አስመልክታ ባወጣችው ወቅታዊ መረጃ አስታውቃለች።
ጳጳሱ ሁለቱም ሳንባቸው በኒሞኒያ ወይም እጥፍ ሳምባ ምች(ደብል ኒሞኒያ) መጠቃት መጀመሩን ያረጋገጠችው ቫቲካን ሮም በሚገኘው ጀመሊ ሆስፒታል የገቡትን የ88ቱን ጳጳስ ህክምና አወሳስቦታል ብላለች።
ደብል ኒሞኒያ በሁለቱም ሳምባዎች ላይ ቃጠሎና ጠባሳ የሚፈጥርና መተንፈስን አስቸጋሪ የሚያደርግ ነው።
ቫቲካን ትናንት ቅዳሜ ባወጣች መግለጫ ደግሞ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት አባ ፍራንሲስ ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ የጤናቸው ሁኔታ መባባሱን እና ለመጀመሪያ ጊዜ ሁኔታቸውን “አስጨናቂ” በማለት ገልጻለች።
የአባ ፍራንሲስ አሁን ባሉበት ሁኔታ ተጨማሪ ኦክሲጅን እና ደም መውሰድ እንደሚያስፈልጋቸው ሮይተርስ ዘግቧል።
ቫቲካን በመግለጫዋ አክላም፤ "የቅዱስ አባታችን ሁኔታ አሁንም አሳሳቢ ነው፤´አሁንም ከአደጋ ውስጥ ናቸው” ብላለች።
የሮማው ጳጳስ አባ ፍራንሲስ በቅርብ አመታት ውስጥ የጤና መቃወስ አጋጥሟቸዋል። ጳጳሱ በወጣነት ዘመናቸው ባጋጠማቸው የሳምባ ምች ምክንያት የተወሰነው የሳምባ ክፍላቸው ተወግዷል።
አሁን ላይ ጳጳጱ ከህዝብ ፊት የሚቀርቡባቸው እስከ ቅዳሜ ያሉት መርሃግሮች የተሰረዙ ሲሆን፤ የዛሬው የእሁድ የፀሎት ስነ ስርዓት ላይ እንደማይገኙም ነው የተገለጸው።
በታተመው የቫቲካን ቀን መቁጠሪያ መሰረት ይፋዊ መርሃግብር የላቸውም።