ትራምፕ የአሜሪካን ከፍተኛ ወታደራዊ መሪ አባረሩ
ፕሬዝደንቱ የአሜሪካ ባህር ኃይልን በመምራት የመጀመሪያዋ ሴት የሆኑትን አድሚራል ሊሳ ፍራንቼቲንና የአየር ኃይል ምክትል አዛዥን ተክተዋል

ትራምፕ ባለፈው አመት የምርጫ ቅስቀሳ በሚያደርጉበት ጊዜ በ2021 የአሜሪካ ጦር ከአፍጋኒስታን ሲወጣ ለተፈጠረው ክስተት ጀነራሎቹን ተጠያቂ አድርገው ነበር
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በከፍተኛ የፔንታጎን አመራሮች ላይ እየወሰዱት ባለው ያልተጠበቀ እርምጃ የጆይት ቺፍ ኦፍ ስታፍ መሪ የሆኑትን የአየር ኃይል ጀነራል ሲ.ኪው. ብራውንን በትናንትናው እለት አባረዋል።
ትራምፕ ትሩዝ በተባለው ማህበራዊ ገጻቸው ከዚህ በፊት የነበሩ አሰራሮችን በመጣስ በጡረታ ተሰናብተው የነበሩትን ሌትናንት ጀነራል ዳን ኬይን የጄነራል ብራውንን ቦታ እንዲተኩ ማጨታቸውን ገልጸዋል።
ፕሬዝደንቱ የአሜሪካ ባህር ኃይልን በመምራት የመጀመሪያዋ ሴት የሆኑትን አድሚራል ሊሳ ፍራንቼቲንና የአየር ኃይል ምክትል አዛዥንም ተክተዋል። በባህር ኃይል፣ በጦሩና በአየር ኃይል ወታደራዊ ተጠያቂነት እንዲሰፍን ወሳኝ ድርሻ ያለውን ዳኛም አባረውታል።
የትራምፕ ውሳኔ በበጀት ቅነሳ፣ በሰራተኛ ማባረርና የትራምፕ "ቅድሚያ ለአሜሪካ"ፖሊሲ በሚኖረው የስምሪት ለውጥ ምክንያት ስጋት ባንዣበበት ፔንታጎን ውስጥ ትርምስ እንዲጀመር አድርጓል።
የፔንታጐን የሲቪል አስተዳደር ከአንዱ አስተዳደር ወደ ሌላኛው ሲቀየር መለዮ የለበሱ የአሜሪካ ጦር አባላት ከፖለቲካ ግንኙነት ስለሌላቸው የሪፐብሊካን ወይም የዲሞክራት ፖሊሲዎች ያስፈጽማሉ።
ብራውን ወታደራዊ መለዮ የለበሰ ከፍተኛ የፕሬዝደንት አማካሪ መሆን የቻለ ሁለተኛው ጥቁር ሲሆን የስልጣን ዘመኑ የሚያበቃው ከሁለት አመታት በኋላ መስከረም 2027 ነበር። የአሜሪካ ባለስልጣናት እንደገለጹት ብራውን የተባረሩት ሴኔቱ በምትካቸውን የሚሾሙትን ከማረጋገጡ በፊት ነው።
አዲሱ የትራምፕ አስተዳደር ብራውንን ጨምሮ ከፍተኛ የፔንታጐን ኃላፋዎችን እንደሚያባርር ሮይተርስ ባለፈው ህዳር ወር ዘግቦ ነበር። የዲሞክራት የምክርቤት አባላት በሪፐብሊካኑ ትራምፕ የተወሰዱ እርምጃዎችን አውግዘዋል።
በሴኔቱ የጦር አገልግሎት ኮሚቴ ውስጥ የሚሰሩ ከፍተኛ የዲሞክራት የሮድ ደሴት ተወካይ ሴናተር ጃክ ሪድ መለዮ የለበሱ መሪዎችን ማባረር የፖለቲካ ታማኝነት ለመሞከር ወይም ከአፈጻጸም ጋር ምንም ግንኙነት ከሌላቸው የብዙኻነትና የጾታ ጉዳዮች ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል ብለዋል።
ሴናተሩ ይህ የትራምፕ እርምጃ የአሜሪካ ወታደሮች ተልዕኮ በሚፈጽሙበት ወቅት ያላቸውን እምነትና ሙያ ሊሸረሽር እንደሚችልም ጠቅሰዋል።
ሌላኛው የማሳቹሴት የዲሞክራት ተወካይ ሴዝ ሞልተን የማባረሩን ተግባር "አሜሪካዊ ያልሆነ፣ አገርወዳድነት የሌለበትና ለወታደሮችና ለብሔራዊ ደህንነት አደገኛ የሆነ ነው" ሲሉ ገልጸውታል።
"ይህ ጦሩን ፖለቲካዊ የማድረግ ስራ ነው" ብለዋል ሞልተን።
ትራምፕ ባለፈው አመት የምርጫ ቅስቀሳ በሚያደርጉበት ጊዜ በ2021 የአሜሪካ ጦር ከአፍጋኒስታን ሲወጣ ለተፈጠረው ክስተት ጀነራሎቹን ተጠያቂ አድርገው ነበር። ይሁን እንጁ ትራምፕ ጀነራል ብራውንን የተኩበትን ምክንያት ይፋ አላደረጉም።