ግንኙነታቸውን ለማደስ የተስማሙት የአሜሪካ እና ሩሲያ ባለስልጣናት ድጋሚ ሊገናኙ ነው
ከፍተኛ ባለስልጣናቱ የዩክሬን ጦርነትን ማስቆም ላይ ትኩረቱን ያደረገ ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል

ፕሬዝዳንት ፑቲን እና የአሜሪካው አቻቸው ይህ ወር ከመጠናቁ በፊት ሊገናኙ እንደሚችሉ መዘገቡ ይታወሳል
የአሜሪካ እና የሩሲያ ከፍተኛ ልኡካን ቡድኖች በመጪዎቹ ሁለት ሳምንታት ውስጥ ድጋሚ እንደሚገናኙ ተነግሯል፡፡
ሶስት አመታት ለሚጠጋ ጊዜ በከፍተኛ ውጥረት ውስጥ የነበሩት ሀገራት ከአመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቻቸው በሚመራ ከፍተኛ ልዑክ ባሳለፍነው ማክሰኞ በሳኡዲ ተገናኝተው መምከራቸው ይታወሳል፡፡
በውይይቱ ላይ ሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ለማስቀጠል እና አምባሳደሮችን ለመለዋወጥ ተስማምተዋል፡፡
ክሬምሊን ባለፈው ሳምንት የተካሄደው የመጀመሪያ ስብሰባ በአብዛኛው በሩሲያ-አሜሪካ ግንኙነት ላይ ያተኮረ መሆኑን ገልጾ፤ በዩክሬን ጦርነት እልባት ላይ ለመድረስ አስፈላጊ ግንኙነት እንደነበር አመላክቷል፡፡
የሩሲያ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሰርጌ ራያባኮቭ ሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ለማሻሻል መስማማታቸውን ተከትሎ ለሁለተኛ ጊዜ እንደሚገናኙ አረጋግጠዋል፡፡
በዚህኛው ዙር ሁለቱን ሀገራት ወክለው የሚሳተፉ ልዑካን ማንነት በግልጽ ባይታወቅም ውይይታቸው የዩክሬን ጦርነት ማስቆምን በተመለከተ አጀንዳ ላይ እንደሚያተኩር ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ንግግር “ሀገራቱ በመርህ ደረጃ በበርካታ ስትራቴጂካዊ እና የሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል፤ የሁለተኛው ዙር ውይይት አላማም በመጀመሪያው ግንኙነት ባልተጠናቀቁ ነጥቦች ላይ ለመምከር ነው” ብለዋል፡፡
አክለውም በስልታዊ መረጋጋት እና የመሳሪያ ቁጥጥር ላይ ውይይት የሚጀመረው በአሜሪካ ፖሊሲ ላይ መሰረታዊ ለውጥ መደረግ ሲጀምር እንደሆነ የተናገሩ ሲሆን፤ በሁለተኛው ዙር ግንኙነት የመካከለኛው ምስራቅ ጉዳይም እንደሚነሳ ጠቁመዋል፡፡
በተያያዘ ሩሲያ በአሜሪካ እና በአውሮፓ እንዳታንቀሳቅስ የታገደባትን የ300 ቢሊየን ዶላር ሀብት ጉዳይ በዩክሬን የጦርነት ማቆም ድርድር ላይ ልታነሳው እንደምትችል ዘገባዎች እየወጡ ነው፡፡
ሩሲያ ይህን እንዳይንቀሳቀስ የታገደ ገንዘብ ለዩክሬን መልሶ ግንባታ እንዲውል እንደመደራደሪያነት ልታቀርብ መሆኑ ተሰምቷል፡፡
ገንዘቡ ሩሲያ በተቆጣጠረቻቸው ስፍራዎች ላይ ከድህረ ጦርነት በኋላ ለመልሶ ግንባታ እንዲውል ፈቃድ ልትሰጥ እንደምትችል ሮይተርስ ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡
የቡድን 7 አባል ሀገራት ከታገደው የሩሲያ ገንዘብ ላይ ለዩክሬን 50 ቢሊየን ዶላር ብድር እንዲሰጣት ባሳለፍነው የፈረንጆቹ አመት ላይ መስማማታቸው ይታወሳል፡፡