እስራኤል በ25 ደቂቃ ውስጥ 122 ቦምቦችን ጋዛ ላይ መጣሏ ተነገረ
እስራኤል ዛሬ ባካሄደችው ድበደባ አንድ ጋዜጠኛን ጨምሮ የ4 ፍልስጤማውያን ህይወት አልፏል
የአየር ድብደባው የተደረገው ሀማስ ሮኬቶችን ወደ እስራኤል ከተሞች ማስወንጨፉን ተከትሎ ነው
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እስራኤል እና ፍልስጤም የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ጥሪ ቢያቀርቡም፤ ሁለቱም ሀይልች ግን የተኩስ ልውውጥ ከማድረግ አልተቆጠቡም።
የእስራኤል ጦር ትናንት ምሽት በ25 ደቂቃ ውስጥ 122 ቦምቦችን ጋዛ ላይ መጣሉን ታይምስ ኦፍ እስራኤል ዘግቧል።
ምሽት 4 ስዓት ገደማ ላይ መጀመሩ የተነገረለት የእስራኤል ጦር የአየር ድብደባ የሀማስ የዋሻ ውስጥ መተላፊያ መረብን ኢላማ ያደረገ መሆኑም ታውቋል።
የእስራኤል ተዋጊ ጄቶች በጋዛ ሰርጥ የሚያደርጉትን የአየር ድብደባ በዛሬው እለትም ቀጥለው እያካሄዱ መሆኑም ተነግሯል።
በዛሬው ድበደባ አንድ ጋዜጠኛን ጨምሮ የ4 ፍልስጤማውያን ህይወት ያለፈ ሲሆን፤ በርካታ መኖሪያ ቤቶች መፍረሳቸውም ተነግሯል።
እስራኤል የአየር ድብደባውን ማድረግ የጀመረቸው በፍልጤም የሚገኘው የሀማስ ሀይል እና ሌሎች የፍልስጤም ታጣቂዎች ሮኬቶችን ወደ እስራኤል ከተሞች ማስወንጨፉን ተከትሎ ሲሆን፤ በሮኬቶቹ ስለደረሰው ጉዳት ግን እስካሁን የተባለ ነገር የለም።
በትናትናው እለትም የእስራኤል የጸጥታ አካላት ለተቃውሞ በወጡ ፍልስጤማውያን ላይ ጥይት ተኩሰው የ4 ሰዎች ህይወት ማለፉ ይታወሳል።
ግጭቱ ከተጀመረ ዛሬ 10ኛ ቀኑን የያዘ ሲሆን፤ በሁለቱም ወገን የበርካቶች ህይወት አልፏል።
በግጭቱ ምክንያት እስካሁን የ220 ፍልስጤማውያን ህይወት ያለፈ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ 63 ህጻናት፣ 34 ደግሞ ሴቶች ናቸው፡፡ 1 ሺህ 500 ፍልስጤማውያን ደግሞ ቆስለዋል።
በእስራኤል በኩል የ12 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ፤ ከእነዚህም 2 ህጻናት ይገኛሉ፡፡ 300 እስራኤላውያን ደግሞ መቁሰላቸው ነው የተነገረው።
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በእስራኤል እና ፍልስጤም መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ እያደረገ ያለው ጥረት ውጤት ማምጣት አልቻለም።
የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ ተወያይቶ መግለጫ እንዳያወጣ አሜሪካ እንቅፋት እየሆነች ነው የተባለ ሲሆን፤ የአሜሪካ ዲፕሎማቶች ለዚህ በምክንያትነት የሚቀርቡት መግለጫ ማውጣት ችግሩን ለማርገብ አይረዳም የሚል ነው።
ፈረንሳይ በበኩሏ አዲስ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደረስ የእስራኤል ጎረቤት ሀገራት ከሆኑት ግብፅ እና ጆርዳን ጋር እየሰራች መሆኑን ያስታወቀች ሲሆን፤ ቻይና በበኩሏ የፈረንሳይን ሀሳብ እንደምትደግፍ አስታውቃለች።