የእስራኤል ጦር ከጋዛ በተጨማሪ ወደ ጎረቤት ሀገር ሊባኖስ መድፎችን መተኮሱን አስታውቋል
እስራኤል በጋዛ የምታደርገውን የአየር ድብደባ ዛሬም የቀጠለች ሲሆን የሟቾች ቁጥርም እየጨመረ ነው
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ተኩስ አቁም እንዲደረግና ለዚህም ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል
የእስራኤል አየር ሀይል በጋዛ ሰርጥ እያካሄደ ያለመውን የአየር ድብደባ በዛሬው እለትም መቀጠሉ ተነግሯል።
በጋዛ እና በእስራኤል ይዞታ ስር በምትገኘው ዌስት ባንክ የሚኖሩ ፍልስጤማውያን የእስራሌልን የአየር ድብደባ በመቃወም በዛሬው እለት የስራ ማቆም አድማ ያደረጉ ሲሆን፤ በርካታ የንግድ ቤቶች መዘጋታቸውም ነው የተነገረው።
የስራ ማቆም አድማው በጋዛ ውስጥ ከሚንቀሰቃሰው ሀማስ እና ፍልስጤምን ከሚያስተዳድረው ፋታህ ድጋፍ አግኝቷል፡፡ አድማው ሁሉንም አይነት ኢኮኖሚያው እንቅስቃሴ እንዲሁም ትምህርት ቤቶችን እስከ መዝጋት የሚደርስ መሆኑም ታውቋል።
የእስራኤል ጦር ከጋዛ ሰርጥ በተጨማሪ ወደ ጎረቤት ሀገር ሊባኖስ መድፎችን መተኮሱንም በዛሬው እለት አስታውቋል።
እስራኤል ወደ ሊባኖስ መድፎችን የተኮሰችው በትናንትናው እለት ከሰሜናዊ ሊባኖስ ወደ እስራኤል ሮኬቶች መተኮሳቸውን ተከትሎ እንደሆነ ተዘግቧል።
በትናትናው እለት ስድስት ሮኬቶች ከሊባኖስ ወደ እስራኤል የተተኮሱ ቢሆንም ድንበር መሻገር እንዳልቻሉ የእስራኤል ጦር አስታውቋል።
ይህንን ተከትሎም እስራኤል የሮኬቶቹ ምንጭ ወደ ሆኑ የሊባስ ስፍራዎች በአጸፋው መድፈፍ መተኮሷን ነው ጦሩ ያረጋገጠው።
በሊባኖስ የሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጊዜያዊ ኃይልም ራሻያ አል-ፎክሃር ወደ ተባለ አካባቢ መድፎች መተኮሳቸውን አረጋገጦ፤ ሁሉም ኃይሎች ሰከን እንዲሉ ጥሪ አቅርቧል።
በተያያዘ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ግጭቱ ከተከሰተ ወዲህ በትናትናው እለት ለሶስተኛ ጊዜ ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ጋር በስልክ መወያየታቸው ታውቋል።
በውይይታቸውም በእስራኤል እና በሀማስ መካከል ተኩስ አቁም እንዲደረግ እንደሚፈልጉ እና ለዚህም ድጋፍ እንደሚያደርጉ መግለጻቸው ተነግሯል።
የእሰራኤል እና ሀማስ ግጭት ከተቀሰቀ ዛሬ ዘጠነኛ ቀኑን የያዘ ሲሆን፤ በእስካሁኑ ግጭትም 61 ህጻናጽን ጨምሮ የ212 ፍልስጤማውያን ህይወት አልፏል።
በተጨማሪም ከ1 ሺህ 500 በላይ ፍልስጤማውያን በግጭቱ ሳቢያ መቁሰላቸውንም ነው ከጋዛ የሚወጡ ሪፖርቶች የሚያመለክቱት።
በእስራኤል በኩል ደግሞ ሁለት ህጻናትን ጨምሮ የ10 እስራኤላውያን ህይወት ያለፈ ሲሆን፤ ከ300 በላይ ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸው ተነግሯል።