እስራኤል ከአማራ ክልል ከ200 በላይ ዜጎቿን ማስወጣቷን አስታወቀች
ዜጎቹ ባለፈው ሳምንት ግጭት ከተቀሰቀሰባቸው የክልሉ ዋና ከተማ ባህር ዳርና ጎንደር መውጣታቸው ተነግሯል
እስራኤል ዜጎቿ የትም ይሁኑ የት ጥበቃ እንደምታደርግ አስታውቃለች
እስራኤል ሀሙስ ዕለት ከአማራ ክልል 200 የሚሆኑ ዜጎቿንና አይሁዳውያንን ማስወጣቷን አስታወቀች።
የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚንስቴርና የጠቅላይ ሚንስቴር ጽ/ቤት በጋራ ባወጡት መግለጫ በክልሉ በተነሳው ግጭት 174 እስራኤላዊያንና ወደ ሀገሪቱ ለመግባት ብቁ የሆኑ ቤተ-እስራኤላዊያን ከጎንደር እንዲወጡ ተደርጓል።
ሌሎች 30 የሚሆኑ ዜጎች ደግሞ ከባህር ዳር መውጣታቸው ተነግሯል።
በአራት በረራዎች ከአማራ ክልል እንዲወጡ የተደረጉት ዜጎች አዲስ አበባ ደርሰዋል ተብሏል። ከአዲስ አበባም ወደ እስራኤል ያቀናሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ኢላይ ኮን እስራኤላዊያኑ ወደ ሀገራቸው ለመመለስ እስኪወስኑ ድረስ በአዲስ አበባ እንደሚቆዩ ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ መቆየትም እንደሚችሉም ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚንስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ እስራኤል ዜጎቿን የትም ይሁኑ የት ጥበቃ እንደምታደርግላቸው መናገራቸውን የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኸን ዘግቧል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ "አጭር፣ ኮሽታ ያልተሰማበትና ውጤታማ" ላሉት ተልዕኮ ለተሳተፉ አካላት ምስጋና ችረዋል።
የፌደራል መንግስት ባለፈው ሚያዚያ ወር የክልል ልዩ ኃይሎችን ለማፍረስና መልሶ ለማደረጃት መወሰኑን ተከትሎ በአማራ ክልል ያለው የጸጥታ ችግር እየተባባሰ መጥቷል።
በዚህም ምክንያት በክልሉ በትጥቅ የታገዘ እንቅስቃሴ መኖሩን የገለጸው መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ማወጁ ይታወሳል።
በክልሉ የተሰማራው የመከላከያ ሰራዊት ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር ግጭት ውስጥ በመግባቱ በክልሉ ትላልቅ መንገዶች ጭምር ዝግ ሆነዋል።
መንግስት ስድስት የአማራ ክልል ከተሞችን ከታጣቂዎች ስጋት ነጻ ማድረጉን እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መጣሉንም አስታውቋል።