ሩሲያ የኒዩክሌር ሙከራን ከሚያግደው አለማቀፍ ስምምነት ወጣች
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የስምምነቱን ማጽደቂያ አዋጅ የሚሽር ህግ ላይ ፊርማቸውን አኑረዋል
ኒዩክሌር የታጠቁት አሜሪካ እና ቻይና ስምምነቱን አላጸደቁም
ሩሲያ የኒዩክሌር ጦር መሳሪያዎች ሙከራን ከሚከለክለው አለማቀፍ ስምምነት መውጣቷ ተገለጸ።
የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንም በዛሬው እለት ሩሲያ ስምምነቱን ያጸደቀችበትን አዋጅ የሚሽር ህግ ላይ ፊርማቸውን ማኖራቸው ነው የተነገረው።
ውሳኔው ሞስኮ የኒዩክሌር ጦር መሳሪያዎችን ለመሞከር መዘጋጀቷን ያሳያል ተብሏል።
በዩክሬን ጦርነት ምክንያት ከዋሽንግተን ጋር የገባችበት ፍጥጫ እያየለ መሄዱን እንደሚያመላክይም ነው ተንታኞች የሚገልጹት።
በፈረንጆቹ 1996 የኒዩክሌር ጦር መሳሪያ እሽቅድምድምን ለመግታት በሚል የመንግስታቱ ድርጅት ይፋ ያደረገው ይሄው ህግ ኒዩክሌር በታጠቁት አሜሪካ እና ቻይና ተፈጻሚ አልሆነም።
ዋሽንግተን ስምምነቱን ብትፈርምም አላጸደቀችውም።
የዛሬው የሞስኮ ውሳኔም አሜሪካን ታሳቢ ያደረገ መሆኑንም የሩሲያ ባለስልጣናት መናገራቸውን ጠቅሶ የዘገበው ሬውተርስ ነው።
ዋሽንግተን የኒዩክሌር ጦር መሳሪያ እስካልሞከረች ድረስ ሞስኮ አውዳሚ መሳሪያዎቿን ዳግም መሞከር እንደማትጀምር ማስታወቋ ተገልጿል።
ፕሬዝዳንት ፑቲን ከወር በፊት ሀገራቸው ለምዕራባውያን ማስጠንቀቂያ መልዕክት ለማስተላለፍ የኒዩክሌር ቦምቦችን እንድትሞክር ከህግ አውጪዎች እና የደህንነት ባለሙያዎች ለቀረበላቸው ጥያቄ ግልጽ ምላሽ ከመስጠት መቆጠባቸው ይታወሳል።
ሩሲያ ከሶቪየት ህብረት መፈራረስ በኋላ የኒዩክሌር ጦር መሳሪያዎችን ሞክራ አታውቅም፤ የሶቪየት ህብረት በ1990 አሜሪካ ደግሞ በ1992 የኒዩክሌር ሙከራ አድርገዋል።
በ21ኛው ክፍለዘመን ከሰሜን ኮሪያ ውጭ የኒዩክሌር መሳሪያዎችን የሞከረ ሀገር የለም ተብሏል።
የአለማችን ቀዳሚዋ የኒዩክሌር ጦር መሳሪያዎች ባለቤት ሀገር ታክቲካል የኒዩክሌር ጦር መሳሪያዎችን በቤላሩስ ማስፈሯ ይታወሳል።
አሜሪካ እና የዩክሬን አጋሮች ለኬቭ እያደረጉት ያለውን የማያቋርጥ ድጋፍ ለመቃወምም በጥቅምት ወር አጋማሽ የባለስቲክ ሚሳኤሎችን መሞከሯ አይዘነጋም።
በየካቲት ወር በፈረንጆቹ 2010 ከአሜሪካ ጋር ከተፈራረመችው የኒዩክሌር ስምምነት የወጣችው ሩሲያ ለ1996ቱ የተመድ ስምምነት ተገዢ አልሆንም ብላለች።
ሞስኮ የኒዩክሌር ጦር መሳሪያ ሙከራ የሚከለክለው ስምምነት ፈራሚ ሆና እንደምትቀጥል ግን አስታውቃለች።