የህክምና ባለሙያ ሆነው ድንገት የእናትዎ አስከሬን እጅዎት ላይ ቢወድቅ ምን ያደርጋሉ?
በጋዛ የአምቡላንስ ረዳት ባለሙያው በእስራኤል ጥቃት የቆሰሉ ሰዎችን ወደ ህክምና ቦታ በማምጣት ላይ እያለ በድንገት የእናቱን አስከሬን አግኝቷል
በእስራኤል የተገደሉ ፍልስጤማዊያን ቁጥር ከ43 ሺህ አልፏል
የህክምና ባለሙያ ሆነው ድንገት የእናትዎ አስከሬን እጅዎት ላይ ቢወድቅ ምን ያደርጋሉ?
ከአንድ ዓመት በፊት የተጀመረው ጦርነት አሁንም የቀጠለ ሲሆን እስራኤል በጋዛ እና በሊባኖስ የአየር ላይ ጥቃቷን ቀጥላለች።
ትናንት ምሽት ላይም በጋዛ ዴር አል ባላህ በተሰኘ አካባቢ ባለ የማጋዚ መጠለያ ጣቢያ ላይ እስራኤል በፈጸመችው ጥቃት 10 ሰዎች ቆስለዋል።
አቤድ ባርዲኒ የተሰኘው ፍልስጤማዊ በየደቂቃው በከባድ መሳሪያ የሚመቱ ሰዎችን የህክምና እርዳታ እንዲያገኙ ከሚያደርጉ ባለሙያዎች መካከል አንዱ ነው።
በዚሁ አካባቢ ባለ አንድ ሆስፒታል ውስጥ የህክምና ድጋፍ የሚፈልጉ ሰዎችን ከአምቡላስ ውስጥ በማውጣት ወደ ሆስፒታል እንዲገቡ በማድረግ ይሰራ የነበረው የህክምና ባለሙያ በድንገት እናቱ በደም ተነክራ እና ህይወቷ አልፎ ያገኛታል።
ሳሚራ የተሰኘችው ይህችን እናት ጨምሮ የህክምና ባለሙያዎች እንደደረሱ የቆሰሉ ሰዎችን ወደ ሆስፒታል የህክምና እርዳታ እንድታገኝ በአምቡላንስ ተወስደው ነበር።
በድንገት ከእናቱ አስከሬን ጋር የተፋጠጠው ይህ የህክምና ባለሙያ ያሳየውን ድንጋጤ የኤኤፍፒ የፎቶግራፍ ባለሙያው ለዓለም አጋርቶታል።
ለፍልስጤም ነጻነት እታገላለሁ የሚለው ሀማስ ከአንድ ዓመት በፊት በእስራኤል ላይ ባደረሰው ያልታሰበ ጥቃት ምክንያት በተቀሰቀሰው በዚህ ጦርነት የተገደሉ ፍልስጤማዊያን ቁጥር ከ43 ሺህ አልፏል።
በእስራኤል በኩል 1 ሺህ 200 ዜጎች ሲገደሉ 200 ዜጎች ደግሞ አሁንም በሀማስ እንደታገቱ ናቸው።
እስራኤል የሀማስ ሀላፊ ያህያ ሲንዋርን መግደሏን ተከትሎ አሜሪካ እና ሌሎች ሀገራት የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲፈረም ጫና በማድረግ ላይ ናቸው።
ከሀማስ ባለፈም የሊባኖሱ ሂዝቦላህ በእስራኤል ላይ ጥቃት በማድረስ ላይ ሲሆን በደቡባዊ ሊባኖስ በኩል የእስራኤል እግረኛ ጦር ውጊያ እያደረጉ ይገኛሉ።
ሀማስ እና ሂዝቦላህ በኢራን ይደገፋሉ በሚል እስራኤል በቴህራን የሀማስ የፖለቲካ ሀላፊ የነበሩት እስማኤል ሀኒየህን ከገደለች በኋላ ኢራን እና እስራኤል የአየር ላይ ጥቃቶችን አድርገዋል።