እስራኤል በጋዛ በፈጸመችው ጥቃት በጥቂቱ የ93 ፍልስጤማውያን ህይወት አለፈ
በቤት ላሂያ ከተማ የሚገኝ ባለ አራት ፎቅ የመኖሪያ ህንጻ በሚሳኤል ተመቶ ፍርስራሹ ነዋሪዎቹን መቅበሩ ተገልጿል
አሜሪካ በርካታ ህጻናት የተገደሉበት ጥቃት “እጅግ አሰቃቂ” ነበር ብላለች
እስራኤል በሰሜናዊ ጋዛ በፈጸመችው ጥቃት የተገደሉ ፍልስጤማውያን ቁጥር 93 መድረሱ ተገለጸ።
በቤት ላሂያ ከተማ በሚገኝ ባለ አራት ፎቅ የመኖሪያ ህንጻ በሚሳኤል ተመቷል።
“በርካታ ሰዎች አሁንም ድረስ በህንጻው ፍርስራሽ ውስጥ ናቸው” ያለው የጋዛ ጤማ ሚኒስቴር፥ ከሟቾቹ ውስጥ ቢያንስ 20 የሚሆኑት ህጻናት መሆናቸውን ገልጿል።
ሁለት እናቶች ከአምስት እና ስድስት ልጆቻቸው ጋር የተገደሉበት የሚሳኤል ጥቃት በሶስት ወራት ውስጥ ከፍተኛው ሞት የተመዘገበበት መሆኑንም ነው ሚኒስቴሩ ያስታወቀው።
በጋዛ ጤና ሚኒስቴር የሚወጣውን የጉዳት አሃዝ በተደጋጋሚ የምታጣጥለው እስራኤል ስለትናንቱ በርካታ ንጹሃንን ስለቀጠፈ የሚሳኤል ጥቃት እስካሁን አስተያየት አልሰጠችም።
የእስራኤል ዋነኛ አጋር አሜሪካ ግን በንጹሃን ፍልስጤማውያን ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት መጨመረ አሳሳቢ ነው ብላለች።
የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃልአቀባይ ማቲው ሚለር ከ90 በላይ ፍልስጤማውያን የተገደሉበትን ጥቃት “አሰቃቂ ጉዳት ያስከተለ ዘግናኝ ጥቃት ነው” ብለውታል።
ቃልአቀባዩ በጥቃቱ ዙሪያ ከእስራኤል ባለስልጣናት ጋር መምከራቸውን ቢጠቅሱም ዋሽንግተን ከ43 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን የተገደሉበት ጦርነት እንዲቀጥል አሁንም ድጋፏን አላቋረጠችም።
ሃማስን ሙሉ በሙሉ ካልደመሰስኩ የጋዛው ጦርነት አይቆምም በሚል አቋሟ የጸናችው እስራኤል ባለፉት ሶስት ሳምንታት በሰሜናዊ ጋዛ ጥቃቷን አጠናክራለች።
ሃማስ መሪው ያህያ ሲንዋር ከተገደለ በኋላ ዳግም ራሱን እንዳያደራጅ በሚል የተጀመረው ጥቃት በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ፍስጤማውያንን አፈናቅሏል።
በጃባሊያ፣ ቤት ላሂያ እና ቤት ሃኑን የሚገኙ ከ100 ሺህ በላይ ሰዎች ከምግብ እርዳታ መቋረጣቸውን የፍልስጤም የአስቸኳይ አደጋ አገልግሎት ከትናንት በስቲያ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
እስራኤል የህክምና ባለሙያዎች ከካማል አድዋን ሆስፒታል እንዲወጡ በማዘዟም የቆሰሉ ሰዎች ምንም አይነት ህክምና እያገኙ አይደለም ተብሏል።
ቴል አቪቭ ባለፉት ሶስት ሳምንታት በሰሜናዊ ጋዛ በፈጸመችው ጥቃት ከ1 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን ህይወት የተቀጠፈ ሲሆን፥ አጠቃላይ ሰብአዊ ቀውሱ እየተባባሰ ይገኛል።
በመንግስታቱ ድርጅት የፍልስጤም የስደተኞች ኤጀንሲ በእስራኤል ፓርላማ የተላለፈበት እግድም የጋዛን ቀውስ ከድጡ ወደማጡ ይወስደዋል ነው የተባለው።