የአሜሪካው ስታርሊንክ ለፍልስጤማዊያን ኢንተርኔት እንዲያቀርብ ተጠየቀ
እስራኤል እግረኛ ጦሯን ወደ ጋዛ ማስገባቷን ተከትሎ በአካባቢው ኢንተርኔት ሙሉ ለሙሉ ተቋርጧል
አሜሪካዊው የኩባንያው ባለቤት ኢለን መስክ ስታርሊንክ በጋዛ ኢንተርኔት እንዲያቀርብ አክቲቪስቶች የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ ጀምረዋል
የአሜሪካው ስታርሊንክ ለፍልስጤማዊያን ኢንተርኔት እንዲያቀርብ ተጠየቀ።
ከ20 ቀናት በፊት ለፍስልጤም ነጻነት እታገላለሁ የሚለው ሐማስ በእስራኤል ላይ ያልታሰበ ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎ በአካባቢው ጦርነት ተቀስቅሷል፡፡
ጋዛን በአየር ስትደበድብ የከረመችው እስራኤል አሁን ደግሞ እግረኛ ጦሯን ወደ አካባቢው ማሰማራቷን አስታውቃለች።
እስራኤል ለምድር ላይ ዘመቻዋ ይረዳት ዘንድ በጋዛ የኢንተርኔት አገልግሎት ሙሉ ለሙሉ እንዲቋረጥ ማድረጓ ተገልጿል።
ይህን ተከትሎም በተለያዩ የዓለማችን ሀገራት የሚገኙ አክቲቪስቶች በዓለማችን ቁጥር አንድ ባለጸጋ ኢለን መስክ የተመሰረተው ስታር ሊንክ ኩባንያ ለፍልስጤማዊያን ኢንተርኔት እንዲያቀርብ በመጠየቅ ላይ ናቸው።
በሳተላይት አማካኝነት ኢንተርኔት በማቅረብ ላይ የሚገኘው ስታር ሊንክ ኩባንያ ለዩክሬናዊያን ኢንተርኔት ማቅረቡ ይታወሳል።
አሁን ደግሞ ልክ እንደ ዩክሬናዊያን ሁሉ ለፍልስጤማዊያን ኢንተርኔት እንዲያቀርብ እነዚህ ተጽዕኖ ፈጣሪ አክቲቪስቶች ዘመቻ መጀመራቸው ተገልጿል።
እስራኤል በጋዛ ላይ እያደረገች ያለው ጥቃት እንዲቆም የተመድ አባል ሀገራት ከደቂቃዎች በፊት በአብላጫ ድምጽ ወስነዋል።
በእስራኤል ጥቃት ምክንያት በየደቂቃው ዜጎች እየተገደሉ ነው የተባለ ሲሆን ከሰባት ሺህ በላይ ፍልስጤማዊያን ተገድለዋል ተብሏል።