ዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት በእስራኤል ላይ ያሳለፈው ውሳኔ ምን ይዟል?
እስራኤል በደቡብ አፍሪካ ከሳሽነት ዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት መከሰሷ ይታወቃል
17 ዳኞች በተሰየሙት ችሎት ፍርድ ቤቱ በትናንትናው እለት በእስራኤል ላይ ውሳኔ አሳልፏል
እስራኤል በጋዛ እየወሰደች ያለውን እርምጃ በቀዳሚነት ከተቃወሙ ሀገራት አንዷ የሆነችው ደቡብ አፍሪካ ወደ ተመድ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ማቅናቷ ይታወሳል።
በዚህም “እስራኤል በጋዛ በሚኖሩ ፍሊስጤማውያን ላይ የዘር ፍጅት እየፈጸመች ነው” ያለችው ደቡብ አፍሪካ፤ ሀገሪቱንም በበዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ከሳለች።
ደቡብ አፍሪካ ለፍርድ ቤቱ ባስገባችው ክስ እስራኤል በጋዛ የሃማስ ቡድን ላይ በወሰደችው እርምጃ በ1948 በወጣው የዘር ማጥፋት ስምምነት የተጣለባትን ግዴታ እየጣሰች መሆኗን ገለጻች።
በሀገራት መካከል የሚነሱ አለመግባባቶችን የሚያስተናግደው ከፍተኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ፍርድ ቤት ደቡብ አፍሪካ በእስራኤል ላይ ባቀረበችው ክስ ላይ በትናናው እለት ብይን ሰጥቷል።
ዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ከሃማስ ታጣቂዎች ጋር ጦርነት በምታደርግበት ወቅት የዘር ማጥፋት ድርጊቶችን ለመከላከል እርምጃ እንድትወስድ ያዘዘ ሲሆን፤ ነገር ግን አፋጣኝ የተኩስ አቁም ጥሪ አላቀረበም።
ፍርድ ቤቱ ምን ደነገገ?
ዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት እስራኤል በዘር ማጥፋትን በሚከለክለው ስምምነት መሰረት ከሚፈፀሙ ድርጊቶች እንድትታቀብ እና ወታደሮቿ በጋዛ የዘር ማጥፋት ወንጀል እንዳይፈፅሙ አዟል።
በደቡብ አፍሪካ በእስራኤል በጋዛ ተፈጽሟል ተብለው የሚታሰቡ አንዳንድ ድርጊቶች እና የህግ ጥሰቶች ውስጥ የተወሰኑት በዘር ማጥፋት ስምምነት ድንጋጌዎች ጥሰቶችን ያስተናገዱ ይመስላሉ ብለዋል የፍርድ ቤቱ ዳኞች።
ብይኑ እስራኤል በጋዛ ፍልስጤማውያን ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል እንዲፈፅም የሚደረጉ ህዝባዊ ቅስቀሳዎችን እንድትከላከልና እንድትቀጣ እንዲሁም የዘር ማጥፋት ወንጀል ከተከሰሱት ማናቸውንም ውንጀላዎች ጋር የተያያዙ ማስረጃዎችን እንድታስቀምጥ አዟል።
እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ውስጥ ያሉትን የፍልስጤም ሲቪሎች ሰብአዊ ሁኔታ ለማሻሻል እርምጃዎችን መውሰድ እንዳለባም ፍርድ ቤቱ አዟል።
ዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት በትእዛዙ ላይ እስራኤል የተኩስ አቁም እንድታደርግ ከማዘዝ ተቆጥቧል።
ሁሉም ዳኞች ውሳኔውን ደግፈዋል?
ዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ጆአን ዶንጉዌን ጨምሮ ከ17 ዳኞች ውስጥ ቢያንስ 15 ዳኞች ውሳኔውን ደግፈው ድምጽ ሰጥተዋል።
ፍርድ ቤቱ ያሳለፋቸውን ስድስት ውሳኔዎች በመቃወም ድምጽ የሰጡት የኡጋንዳ ዳኛ ጁሊያ ሴቡቲንዴ ብቻ ናቸው የተባለ ሲሆን፤ የእስራኤል ጊዜያዊ ዳኛ አሮን ባራቅ ከስድስቱ ውሳኔዎች አረቱን በመቃወም ድምጽ ሰጥተዋል።
በቀጣይ ምን እርምጃ ይጠበቃል?
እስራኤል ዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት ውሳኔ ካሳለፈበት ጊዜ አንስቶ በአንድ ወር ውስጥ ትእዛዙን ለመፈጸም የወሰደቻቸውን እርምጃዎች ሪፖርት ማቅረብ ይጠበቅባታል።
ፍርድ ቤቱ የጉዳዩን ትክክለኛነት በዝርዝር የሚመረመር ሲሆን፤ ይህ ሂደት ዓመታት ሊወስድ እንደሚችልም ተነግሯል።