የእስራኤልና ሃማስ የተኩስ አቁም ድርድር ዛሬ በካይሮ ዳግም ይጀመራል
አሜሪካም የሀገሪቱን የስለላ ድርጅት (ሲአይኤ) ዳይሬክተር ቢል በርንስ ወደ ግብጽ ልካለች
ሃማስ በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት ከፈጸመ ዛሬ ስድስት ወር ደፍኗል
የእስራኤልና ሃማስ የተኩስ አቁም ድርድር ዛሬ በግብጽ መዲና ካይሮ ዳግም እንደሚጀመር ተገልጿል።
ሃማስም በጋዛ ምክትል መሪውን ካሊል አል ሃያ የተመራ ልኡክን ዛሬ ወደ ካይሮ እንደሚልክ ያስታወቀ ሲሆን፥ የአሜሪካው የስለላ ድርጅት (ሲአይኤ) ዳይሬክተር ቢል በርንስ በንግግሩ ላይ ለመሳተፍ ትናንት ምሽት ካይሮ ገብተዋል።
የኳታሩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሼክ መሀመድ ቢን አብዱልራህማን አልታኒም እና የእስራኤል ተደራዳሪዎችም ዛሬ ካይሮ ገብተው የተኩስ አቁም ድርድሩ እንደሚጀመር የግብጹ አል ቃሄራ ቴሌቪዥን ዘግቧል።
ሃማስ ወደ እስራኤል ዘልቆ ድንገተኛ ጥቃት ካደረሰ ዛሬ ድፍን ስድስት ወራት ተቆጥረዋል።
እስራኤል ከ1 ሺህ 100 በላይ ዜጎቿን ላጣችበት ጥቃት በወሰደችው የአጻፋ እርምጃ ከ33 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን ህይወት ተቀጥፎ፤ ከ75 ሺህ በላይ ንጹሃን ቆስለዋል።
በአጭር ጊዜ ሃማስን እደመስሳለሁ ያለው የቤንያሚን ኔታንያሁ አስተዳደር ከስድስት ወራት በኋላም ዘመቻው ሙሉ ግቡን ስላልመታለት ጦርነቱ እንደሚቀጥል ሲገልጽ ይደመጣል።
የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክርቤት በጋዛ በአስቸኳይ ተኩስ እንዲቆም የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ ቢያጸድቅም ደም አፋሳሹና ጋዛን እያፈራረሰ ያለው ጦርነት በአጭር ጊዜ የሚቋጭ አይመስልም።
በኳታርና ግብጽ አደራዳሪነት በህዳር ወር ከተደረሰው ጊዜያዊ ተኩስ አቁምና የታጋቾችና እስረኞች ልውውጥ በኋላ በካይሮ፣ በዶሃ እና ፓሪስ የተካሄዱ ምክክሮች ውጤት አላስገኙም።
ዛሬ በካይሮ በሚጀመረው ድርድር ግን እስራኤል የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንድትደርስ ከአጋሯ አሜሪካ ጭምር ግፊት ይደረግባታል ብሏል ሬውተርስ በዘገባው።
ሃማስ ግን ቀደም ሲል ባቀረበው ለስድስት ሳምንት ተኩስ ቆሞ 40 ታጋቾች ለመልቀቅና እስራኤል በምትኩ ፍልስጤማውያን እስረኞችን እንድትፈታ የሚጠይቅ ምክረሃሳብ ላይ ለውጥ አለማድረጉን ገልጿል።
የእስራኤል ጦር ከጋዛ እንዲወጣና የተፈናቀሉ ፍልስጤማውያንም ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ የሚጠይቀውን የሃማስ ምክረሃሳብ እስራኤል በፍጹም እንደማትቀበለው አስታውቃለች።
እስራኤላውያን ስድስት ወራት በደፈነው የጋዛው ጦርነት ዙሪያ በሁለት ጎራ ተከፍለዋል፤ ሃማስ ያደረሰውን ጉዳት የሚያወሱና ለእስራኤል ህልውና አደገኛ ነው የሚሉ እስራኤላውያን ከኔታንያሁ ጎን ቆመዋል።
ታጋቾችን በአጭር ጊዜ ማስለቀቅ አልቻለም፤ ጦርነቱ የእስራኤልን አለማቀፍ ክብር ዝቅ አድርጓል የሚሉ እስራኤላውያን ደግሞ አደባባይ በመውጣት ኔታንያሁ ስልጣን እንዲለቁ ሲጠይቁ ከርመዋል።
የፍልስጤማውያን እልቂት፣ የጋዛ መፈራረስና የንጹሃን መሸሸጊያ ማጣት ባለፉት 180 ቀናት የየእለቱ አለማቀፍ ዜና ቢሆንም እስራኤል ጦርነቱ በራፋህ እንዲቀጥል እቅድ አጽድቃለች። “ካልደመሰስኩት ከጋዛ አልወጣም” ከምትለው ቡድን ጋር የምታደርገው ድርድርም ውጤት ያመጣል ተብሎ አይጠበቅም።