የጋዛው ጦርነት በኔታንያሁ እና በቀጣዩ የአሜሪካ ምርጫ ምን ተጽዕኖ ይኖረዋል?
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር የአሜሪካ ሪፐብሊካን ሴናተሮች ላቀረቡላቸው ጥያቄዎች በበይነ መረብ ምላሽ ሲሰጡ ጦርነቱ ይቀጥላል ብለዋል
በሪፐብሊካኖች ድጋፍ ያላቸው ኔታንያሁ በዴሞክራቶች ተከታታይ ወቀሳ እየቀረበባቸው ነው
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ስድስተኛ ወሩን ሊደፍን የተቃረበው የጋዛ ጦርነት እንደሚቀጥል ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአሜሪካ ሪፐብሊካን ሴናተሮች ላነሱላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ ጦርነቱ በአጭር ጊዜ እንደማይቆም አመላክተዋል።
የትናንቱ የቪዲዮ ውይይት አሜሪካ በእስራኤል ላይ የያዘችው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በዴሞክራቶች እና ሪፐብሊካኖች የሚሰጠው ትርጓሜ እየተራራቀ መሄዱን ያሳያል ተብሏል።
ዴሞክራቱና በሴኔቱ የአብላጫ ድምጽ መሪው ቹክ ሹመር ባለፈው ሳምንት፥ እስራኤል በጋዛው ጦርነት ምክንያት አለማቀፍ ስሟ እየጠለሸ ነው ማለታቸው ይታወሳል።
ሹመር እስራኤላውያን ኔታንያሁን ከስልጣን እንዲያነሱ ጥሪ ማቅረባቸውና ፕሬዝዳንት ባይደንም የሹመርን ሃሳብ በርካታ አሜሪካውያን ይጋሩታል ማለታቸው አይዘነጋም።
ወግ አጥባቂው ኔታንያሁ ከሪፐብሊካኖች ጋር የረጅም ጊዜ ወዳጅነት አላቸው፤ ዶናልድ ትራምፕ በ2016 ዋይትሃውስ እንደገቡ የአሜሪካን የረጅም ጊዜ ፖሊሲዎች መሻራቸው ይታወሳል።
“እየሩሳሌም የእስራኤል መዲና ናት፤ የጎላን ተራሮችም የእስራኤል ይዞታዎች ናቸው፤ እስራኤል በሃይል በያዘቻቸው ስፍራዎች የምታካሂደው የሰፈራ ፕሮግራምም ህጋዊ ነው” የሚሉት ንግግሮቻቸውም ፍልስጤማውያንን ያስቆጣ ነበር።
በያዝነው የፈረንጆቹ አመት የሚደረገው የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የጋዛው ጦርነት የዴሞክራቶችና ሪፐብሊካኖች መሻኮቻ ሆኗል።
ትራምፕ በቅርቡ ባደረጉት የምርጫ ቅስቀሳ “አይሁዳውያን ለዴሞክራቶች ድምጽ ከሰጡ ሀገራቸውንና ሃይማኖታቸውን አያከብሩም ማለት ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
በትናንትናው የበይነ መረብ ምክክር የተሳተፉ የሪፐብሊካን ሴናተሮች ኔታንያሁ በጋዛ የጀመረውን ጦርነት እስከመጨረሻው እንዲገፋበት ደግፈዋል ብሏል ሬውተርስ በዘገባው።
ዴሞክራቶችም ቢሆኑ የእስራኤል ጥቃት ፍልስጤማውያን መጠበቅ አልቻለም፤ ሰብአዊ ድጋፍም በብዛት እየገባ አይደለም ከሚለው ተቃውሟቸው ውጪ ጦርነቱ እንዲቆም አይፈልጉም።
የባይደን አስተዳደር በጸጥታው ምክርቤት ድምጽን በድምጽ የመሻር መብቷን ተጠቅማ የቀረቡ የተኩስ አቁም የውሳኔ ሃሳቦችን ደጋግማ ውድቅ ማድረጉ የሚታወስ ነው።
ዴሞክራቶችም ሆኑ ሪፐብሊካኖች በቀጣዩ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ድምጽ ለማግኘት ከሚያደርጉት ፉክክር ጋር ተያይዞ ኔታንያሁን ሸንቆጥ ቢያደርጉም አሜሪካ የእስራኤል ሁነኛ አጋር መሆኗን አሃዛዊ መረጃዎች ያመላክታሉ።