የመንግስታቱ ድርጅት የተኩስ አቁም ስምምነቱ መጠነኛ ለውጥ ቢያመጣም የሰብአዊ ቀውሱ አሳሳቢ ነው ብሏል
እስራኤልና ሃማስ ለአራት ቀናት የደረሱትን የተኩስ አቁም ስምምነት ለ48 ስአታት ለማራዘም መስማማታቸውን ኳታር አስታውቃለች።
በተራዘመው የተኩስ አቁም ስምምነት 20 እስራኤላውያን ታጋቾች እና 60 ፍልስጤማውያን እስረኖችን ለመልቀቅ ስምምነት ላይ መደረሱንም ነው አደራዳሪዋ ዶሃ የገለጸችው።
ባለፉት አራት ቀናት 219 እስረኞች እና ታጋቾች የተለቀቁበት ስምምነት ለፍልስጤማውያን ብሎም ቤተሰቦቻቸውን በመጠባበቅ ላይ ለሚገኙ እስራኤላውያን ትልቅ የምስራች ቢሆንም ጦርነቱ መቀጠሉ አይቀርም የሚለው ስጋት ግን እንዳየለ ነው።
እስራኤል በአራት ቀናት ውስጥ ያስለቀቀቻቸው ታጋቾች ቁጥር 50 ነው፤ ሌላ ስምምነት እስካልተደረሰ ድረስ ቀሪዎቹን በሃማስ የታገቱ ሰዎችን ለማስለቀቅ 20 ቀናት ያስፈልጋሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ሃማስ በየእለቱ በአማካይ 10 ታጋቾችን የሚለቅ ከሆነ ታጋቾቹ ተለቀው እስኪያልቁ ድረስ የተኩስ አቁሙን ማስቀጠል ይቻላል ማለታቸው የሚታወስ ነው።
ይሁን እንጂ ስምምነቱ ለሁለት ቀናት ብቻ መራዘሙ በእስራኤላውያን እና ዜጎቻቸው በታገቱባቸው ሀገራት ዘንድ ከፍተኛ ስጋት መፍጠሩን ነው ፍራንስ 24 የዘገበው።
ባለፉት አራት ቀናት የጥይት ድምጽ ያልሰሙት የጋዛ ነዋሪዎች ከ14 ሺህ 500 በላይ ፍልስጤማውያንን ህይወት የቀጠፈው ጦርነት ዳግም መቀስቀሱ አይቀሬ ነው የሚለው ስጋታቸውም እንዳለ ነው።
ታጋቾቹ ከሃማስ ባሻገር በተለያዩ ታጣቂዎች እጅ መያዛቸው መነገሩም የተኩስ አቁም ስምምነቱን ለማራዘም አዳጋች ሁኔታ ሊፈጥር እንደሚችል ሬውተርስ ዘግቧል።
የኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ የአራት ቀናት የተኩስ አቁም ስምምነቱን ለማስፈጸም በርካታ መሰናክሎች እንደነበሩ በማውሳት፥ የተኩስ አቁም ስምምነቱን ዘለግ ላለ ጊዜ ለማራዘም ጥረቶች መቀጠላቸውን ገልጿል።
እስራኤል ሃማስን ካልደመሰስኩና ሁሉም ታጋቾች ካልተለቀቁ ጦርነቱ አይቆምም በሚለው አቋሟ መጽናቷን ኔታንያሁ በጋዛ ድንበር ከወታደሮቻቸው ጋር ሲገናኙ ያደረጉት ንግግር አመላክቷል።
የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ሁለት ጊዜ በእስራኤል ጉብኝት ያደረጉት የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን የተኩስ አቁሙ በሚራዘምበት ሁኔታ ለመምከር ወደ ቴል አቪቭ ያቀናሉ ተብሏል።
በኳታር፣ ግብጽ እና አሜሪካ ሸምጋይነት የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነትን ተከትሎ ከ200 በላይ የሰብአዊ ድጋፍ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ወደ ጋዛ እንደሚገቡ መገለጹ ይታወሳል።
ስምምነቱ በርካታ ተሽከርካሪዎች ወደ ጋዛ እንዲገቡ ቢያደርግም በሰርጡ ያለው የሰብአዊ ቀውስ አፋጣኝ ምላሽን የሚሻ ነው ሲል የመንግስታቱ ድርጅት አሳስቧል።