እስራኤልና ሃማስ በሁለተኛው ምዕራፍ የተኩስ አቁም ዙሪያ በካይሮ ድርድር ጀመሩ
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በነገው እለት የሚጠናቀቀውን የመጀመሪያ ምዕራፍ የተኩስ አቁም የሚያስቀጥል ስምምነት ይደረሳል ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል

የትራምፕ የመካከለኛው ምስራቅ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ በቀጣይ ቀናት ወደ ቀጠናው ያመራሉ ተብሏል
እስራኤል እና ሃማስ በሁለተኛው ምዕራፍ የጋዛ ተኩስ አቁም ዙሪያ ስምምነት ላይ ለመድረስ በግብጽ ድርድር መጀመራቸው ተነገረ።
የአሜሪካ እና ኳታር አደራዳሪዎችም በካይሮው ድርድር እየተሳተፉ መሆኑን የግብጽ ብሄራዊ የመረጃ አገልግሎት አስታውቋል።
በጥር 19 2025 ተግባራዊ የሆነው የመጀመሪያው ምዕራፍ የተኩስ አቁም በነገው እለት ይጠናቀቃል።
በሁለተኛው ምዕራፍ ተኩስ አቁም ዙሪያ ቀደም ብሎ በኳታር ሊካሄድ የነበረው ድርድር በተለያዩ ምክንያቶች መራዘሙ ይታወሳል።
እስራኤልና ሃማስ በካይሮው ድርድር ስምምነት ላይ የሚደርሱ ከሆነ በጋዛ ከሚገኙ ቀሪ 59 ታጋቾች በህይወት ያሉት (24ቱ) በሁለተኛው ምዕራፍ ይለቀቃሉ።
የጋዛውን ጦርነት ሙሉ በሙሉ እንደሚያስቆም በሚጠበቀው ምዕራፍ እስራኤል ወታደሮቿን ከጋዛ አስወጥታ የሰብአዊ ድጋፍ በስፋት እንዲገባ ይደረጋል።
የእስራኤል ባለስልጣን የካይሮው ድርድር ከመጀመሩ ከስአታት በፊት የሰጡት አስተያየት ግን ጥርጣሬ ፈጥሯል። ባለስልጣኑ እስራኤል ከስትራቴጂካዊው "ፊላደልፊያ ኮሊደር" ወታደሮቿን አታስወጣም ማለታቸውን አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
ጋዛን ከግብጽ የሚያዋስነው የፊላደልፊያ መተላለፊያ ሃማስ የጦር መሳሪያዎችን አስርጎ የሚያስገባበት መሆኑን ቴል አቪቭ በተደጋጋሚ ትወቅሳለች።
ካይሮ በበኩሏ በግዛቷ በኩል ያለውን በውስጥ ለውስጥ የተሰራ የመሳሪያ ማስተላለፊያ ዋሻ ከአመታት በፊት ማውደሟን ትገልጻለች። በአካባቢው ከጦርነት ነጻ የሆነ ቀጠና በመክፈት የጦር መሳሪያ ዝውውር እንዳይኖር እንደምትቆጣጠርም በማከል።
ሃማስ ደግሞ እስራኤል ከመተላለፊያው ካልወጣች የተኩስ አቁም ስምምነቱን እንደጣሰች ይቆጠራል። በዚህ አቋሟ ከጸናችም በጋዛ የሚገኙ ታጋቾችን አለቅም ብሏል።
እስራኤል ከነገ ጀምሮ በስምንት ቀናት ውስጥ ከፊላደልፊያ ኮሊደር ጦሯን ማስወጣት ቢኖርባትም "ሃማስን እደመስሳለሁ" የሚል ተደጋጋሚ ዛቻውን የሚያሰማው የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ አስተዳደር ጦር የማስወጣቱን ጉዳይ ይቀበለዋል ተብሎ አይጠበቅም።
እስራኤል ጦርነቱን ዳግም ሳትጀምር ሃማስን እንዴት መደምሰስ ትችላለች የሚለው ጉዳይ ግን ግልጽ አይደለም።
የኔታንያሁን የሃማስን ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ አቅም የማንኮታኮት እቅድ የሚደግፉት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግን በካይሮው ድርድር ስምምነት ላይ ይደረሳል ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።
ትራምፕ የመካከለኛው ምስራቅ ልዩ መልዕክተኛቸውን ስቲቭ ዊትኮፍ በቀጣይ ቀናት ወደ ቀጠናው እንደሚልኩም ሬውተርስ ዘግቧል።