እስራኤል በሃማስ የታገቱ ሰዎችን ለማስለቀቅ ከ11 ሺህ በላይ እስረኞችን ትፈታለች?
ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ የሃማስ እስረኞችን ለቀው ከ24 ቀናት በፊት የታገቱ እስራኤላውያንን እንዲያስፈቱ ጫናው በርትቶባቸዋል
ቴል አቪቭ ከዚህ ቀደም ከሃማስ እና ሄዝቦላህ ጋር እስረኛ ለመለዋወጥ ስምምነት ማድረጓ ይታወሳል
የፍልስጤሙ ሃማስ ያገታቸውን ከ220 በላይ እስራኤላውያን ለመልቀቅ በእስራኤል የታሰሩ ፍልስጤማውያን እንዲለቀቁለት ቅድመ ሁኔታ አስቀምጧል።
በሃማስ ቤተሰቦቻቸው የታገቱ እስራኤላውያን ተወካዮችም ወደ ፕሬዝዳንት ኢሳቅ ሄርዞግ ቢሮ አምርተው የታጋቾቹ ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጠውና የትኛውም ዋጋ ተከፍሎ ቤተሰቦቻቸው እንዲለቀቁ ጠይቀዋል።
ጦርነቱን የማቆምም ሆነ ታጋቾቹን ለሃማስ ጥያቄ ምላሽ በመስጠት የማስለቀቅ ፍላጎት ያላሳየው የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ አስተዳደር ጫናው በዝቶበታል።
ሃማስ ባላፈው ሳምንት ካገታቸው ሰዎች ውስጥ 50 የሚሆኑት በእስራኤል የአየር ድብደባ ተገድለዋል ማለቱም የታጋቾቹን ቤተሰቦች ይበልጥ ጭንቅ ውስጥ ከቷል።
ሃማስ ከ24 ቀናት በፊት በእስራኤል ላይ ያልተጠበቀ ጥቃት ከመፈጸሙ በፊት 5 ሺህ 192 ፍልስጤማውያን በእስራኤል እስር ቤቶች ውስጥ ታስረው እንደሚገኙ ሃሞክድ የተሰኘው የእስራኤል ግብረሰናይ ድርጅት ይገልጻል።
ከነዚህ ውስጥ 1 ሺህ 319ኙ ያለምንም ክስ በእስር ላይ የሚገኙ ናቸው።
ከጥቅምት 7ቱ ጥቃት በኋላም 1 ሺህ 680 ፍልስጤማውያን በዌስትባንክ እና ምስራቅ እየሩሳሌም መታሰራቸውን ሃማስ የሚገልጸው።
እስራኤል መግባት የሚያስችል ፈቃድ ያላቸው ከ4 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን መታሰራቸውም በእስራኤል ከሃምስ ጋር በተያያዘ በእስር ላይ የሚገኙ ፍልስጤማውያንን ቁጥር 11 ሺህ ያደርሰዋል።
የእስራኤል ጦር በትናንትናው እለት በዌስትባንክ ከሃማስ ጋር ግንኙነት አላቸው ያላቸውን 700 ፍልስጤማውያን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል።
እስራኤል ከፍልስጤሙ ሃማስ እና ከሊባኖሱ ሄዝቦላህ ጋር ከዚህ ቀደም እስረኛ የመለዋወጥ ስምምነት ላይ መድረሷን ቢቢሲ በዘገባው ያወሳል።
በጋዛ ከፈረንጆቹ 2006 እስከ 2011 በሃማስ ታስሮ የቆየውን ጂላድ ሻሊት የተባለ ወታደሯን ለማስፈታት 1 ሺህ 27 ፍልስጤማውያን እስረኞችን ስትለቅም ቤንያሚን ኔታንያሁ ጠቅላይ ሚኒስትር ነበሩ ይላል።
በወቅቱ የተለቀቁት እስረኞች 600 ለሚጠጉ እስራኤላውያን ህልፈት ተጠያቂ ናቸው በሚልም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ ሲያስነሳ መቆየቱን ነው ዘገባው ያስታወሰው።
አብዛኞቹ ከ12 አመት በፊት የተለቀቁት የሃማስ እስረኞች በእስራኤል ዳግም መታሰራቸው የተነገረ ሲሆን፥ አሁን ላይ የኔታንያሁ አስተዳደር የቀደመ ስህተቱን አይደግምም የሚሉ ተንታኞች አሉ።
ይሁን እንጂ የታጋቾቹ ቤተሰቦች ለሀገራቸው መንግስት ከሃማስ ጋር የእስረኞች ልውውጥ ስምምነት እንዲደረስ መወትወታቸውን ቀጥለዋል።
ቴል አቪቭ ግን የታገቱት ዜጎች የሚፈቱት ሃማስን ሙሉ በሙሉ በመደምሰስ እንጂ እስረኞችን በመልቀቅ አይደለም እያለች ነው።