ወደ ሁለተኛው ምእራፍ ተሸጋግሯል በተባለው የእስራኤል ሃማስ ጦርነት የተፈጠሩ አዳዲስ ክስተቶች ምንድናቸው?
በሰሜን ጋዛ በእስራኤል ጦርና በሃማስ ታጠቂዎች መካከል ውጊያ እየተካሄደ ነው
እስራኤል በጋዛ እየፈጸመች ባለው ድብደባ የሞቱ ፍሊስጤማውያን ቁጥር ከ8 ሺህ አልፏል
ሃማስ ወደ እስራኤል ያልተጠበቀ ጥቃት ከፈጸመ 23 ቀናት ተቆጥረዋል።
እስራኤል ወደ ሁለተኛ ምእራፍ ተሸጋግሯል ባለችው የመልሶ ማጥቃት እርምጃ በእግረኛ ጦር፣ በብረት ለበስ እና በአየር አጠናክራ ቀጥላለች።
ሌሊቱን በጋዛ ከተማ ከፍተኛ የአየር ድብደባዎች ነበሩ የተባለ ሲሆን፤ በደቡብ ምእራብ ጋዛ የሚገኙት እየሩሳሌም ሆስፒታል እና የቱርክ ሆስፒታሎች ዋነኛ ኢላማ ነበሩ።
በጋዛ ከተማ ሌሊቱን በመኖሪያ ቤቶች ላይ በተፈጻመ የአየር ድብደባ ብቻ ብትንሹ 20 ሰዎች መሞታቸው ተነግሯል።
በሰሜን ጋዛ በእስራኤል ጦር እና በሃማስ ታጠቂዎች መካከል ውጊያ እየተካሄደ ሲሆን፤ በተለይም በሰሜን ጋዛ በተለያዩ ግንባሮች ውጊያው ተጠናክሮ ቀጥሏል።
የእስራኤል ጦር ፍሊስጤማውያን አል ቁዱስ ሆስፒታል አካባቢ ለቀው እንዲወጡ ማሳቧን ተከትሎ፤ በርካታ ታማሚዎች መሸሻቸው እና ሌሎችም ስጋት ላይ መውደቃቸው ተስምቷል።
በእስራኤል የአየር ድብደባ የሞቱ ፍሊስጤማውያን ቁጥር ከ8 ሺህ ማለፉን የፍሊስጤም ባለስልጣናት አስታውቀዋል።
የተመድ የህጻናት አድን ድርጅት ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ በጋዛ የተገደሉ ህጻት ቁጥር 3 ሺህ 195 መድረሱን እና ይህም በዓለም ዙሪያ በየዓመቱ በግጭቶች ከሚሞቱ ህጻናት ቁጥር በላይ መሆኑን አስታውቋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በትናንትናው አልት ሰብዓዊ እርዳታ የጫኑ 33 ተሸከርካሪዎች በግብጽ በኩል ጋዛ መግባታቸውን አስታውቋል።