የደቡብ አፍሪካ ምክር ቤት በፕሪቶሪያ ያለው የእስራኤል ኢምባሲ እንዲዘጋ ውይይት እንደሚያደርግ ተገልጿል
እስራኤል በጋዛ ላይ በፈጸመችው ጥቃት በጦር ወንጀል እንድትከሰስ ክስ ቀረበባት።
ሃማስ በእስራኤል ላይ ድንገተኛ እና ያለተጠበቀ ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎ የተቀሰቀሰው ጦርነት ከተጀመረ 43ኛ ቀኑን ይዟል።
እስራኤልም ራሴን ለመከላከል በሚል የአጸፋ እርምጃ ለመውሰድ ጋዛ ላይ ድብደባ ከጀመረች 43 ቀናት የተቆጠሩ ሲሆን፤ በእስራኤል ጦርና በሃማስ ታጣቂዎች መካከል የተቀከቀሰው ጦርነትን እንደቀጠለ ይገኛል።
በርካታ ሀገራት እስራኤል የጀመረችውን ጥቃት እንድታቆም ግፊት በማድረግ ላይ ቢሆኑም በጋዛ ላይ እየደረሰንያለው ጥቃት ግን እንደቀጠለ ነው።
እስራኤል ጥቃቷን አለማቆሟን ተከትሎ ደቡብ አፍሪካ ጉዳዩን ወደ ጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት መውሰዷን አስታውቃለች።
የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎዛ እንዳሉት "እስራኤል በፍልስጤማዊያን ላይ እያደረሰች ላለው ጥቃት ልትጠየቅ ይገባል" ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ራማፎዛ ኳታርን በጎበኙበት ወቅት እንዳሉት "ሀማስ በእስራኤል ላይ ያደረሰውን ጥቃት አላወገዝንም፣ ቢሆንም ግን አሁን በጋዛ ግዛት ነዋሪዎች ላይ እየደረሱ ያሉ ጥቃቶችን እንዳናወግዝ አያደርግም" ሲሉም ጠቅሰዋል።
ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ፍርድ ቤት ጉዳዮን እንደሚመረምር እና የእስር ማዘዣ እንደሚያወጣ እናምናለንም ሲሉ ፕሬዝዳንት ራማፎዛ ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የደቡብ አፍሪካ ህግ አውጪ ምክር ቤት በፕሪቶሪያ ያለው የእስራኤል ኢምባሲ ይዘጋ በሚለው ጉዳይ ዙሪይ ውይይት እንደሚያደርግ ተገልጿል።
ምክር ቤቱ ከኢምባሲው በተጨማሪም ደቡብ አፍሪካ ከእስራኤል ጋር ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሙሉ ለሙሉ እንዲቋረጥም ይወያያል ሲል ኤኤፍፒ ዘግቧል።
በእስራኤል-ጋዛ ጦርነት ምክንያት ከ11 ሺህ በላይ ፍልስጤማዊያን ሲገደሉ ሁለት ሺህ ገደማ እስራኤላዊያንም መገደላቸው ተገልጿል።
አሜሪካ ለእስራኤል በቀጥታ የጦር መሳሪያ እና ገንዘብ ድጋፍ ያደረገች ሲሆን ኢራን፣ ቱርክ፣ ኳታር፣ ሳውዲ አረቢያ እና ሌሎችም ሀገራት ደግሞ ሀማስን በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ ይደግፋሉ ተብሏል።