ከ1 ሚሊየን በላይ ፍልስጤማውያን ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸውን ተመድ ገለጸ
ሃማስ ባሳለፍነው ሳምንት ቅዳሜ በእስራኤል ላይ ያለተጠበቀ እና ድንገተኛ ጥቃት መሰንዘረሩን ተከትሎ በእስራኤልና በፍልስጤም መካከል የተጀመረው ጦርነት እንደቀጠለ ነው።
እስራኤል አዳሩን ጋዛ ከተማን በአየር ስትደበድብ ያደረች ሲሆን፤ እስራኤል በወሰደቸው የአየር ድብደባ ጥቃት ባለፉት ጥቂት ሰዓታት ብቻ በርካታ ፍልስጤማውያን መሞታቸው ታውቋል።
በእስራኤል አየር ድብደባ ከ1 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን በፈራረሱ ህንጻዎች ስር መጥፋታቸውን የፍስጤም የሲቪል መከላከያ ቡድን አስታውቋል።
በህንጻች ፍርስራሽ ሰር ካሉት ውስጥ የሞቱ እና የቆሰሉ ሰዎች እንደሚገኙበትም ቡድኑ ገልጿል።
በእስራኤል ጋዛ አዳሩን የተፈጸሙ ጉዳዮች
የእስራኤል ጦር በጋዛ ላይ "በአየር፣ በባህር እና በየብስ በተቀናጁ ጥቃቶች" ለማስፋፋት በተጠንቀቅ ላይ ነው።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ስራኤል ጦሯን አስገብታ ጋዛን ለመቆጣጠር ከወሰነች “ትልቅ ስህተት ነው” ብለዋል።
የጋዛ ባለስልጣናት በፍልስጤም ሁለት የሲቪል መከላከያ ቢሮዎች ላይ የአየር ድብደባ በመፈጸም 7 ሰዎችን መግደላቸውን ተከትሎ እስራኤልን በጦር ወንጀል ከሰዋል።
በፍሊስጤም ጋዛ እና በግብጽ መካከል ያለው የራፋ መሻገሪያ ዛሬ ጠዋት ከ3 ሰዓት ጀምሮ ለጥቂት ሰዓታት እንደሚከፈት እና በዚህም የውጭ ሀገራት ዜጎች ወደ ግብጽ እንዲሻገሩ ይደረጋል ተብሏል።
የራፋ መሻጋገሪያ ድንበርን ለመከፍት እንዲቻልም በደቡባዊ ጋዛ የተኩስ አቁም እንዲደረግ በእስራኤል፣ አሜሪካና ግብጽ መካከል ስምምነት መደረሱ ተነግሮ ነበር።
ሃማስ ስለ ሰብዓዊ የተኩስ አቁም ስምምነት ምንም መረጃ የለኝም ብሏል
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁም የውጭ ዜጎችን ለማስወጣት በሚል የሚደረግ የሰብዓዊ የተኩስ አቁም የለም ብለዋል።
እየተካሄደ ባለው ጦርነት ከ1 ሚሊየን በላይ ፍልስጤማውያን ከጋዛ መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል።
የሟቾች ና ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ቁጥር
በሃማስ ጥቃት እና በእስራኤል የአየር ድብደባ ከሁለቱም ወገኖች የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ4 ሺህ ማለፉ ተነግሯል።
የፍልስጤም ጤና ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ሴቶች እና ህጻናትን ጨምሮ 2 ሺህ 670 ሰዎች በጋዛ በደረሰው የአየር ጥቃት ተገድለዋል። 9 ሺህ 600 በላይ የሚሆኑት ደግሞ የመቁሰል አደጋ እንደደረሰባቸው ሚኒስቴሩ ገልጿል።
ከባለፈው ቅዳሜ ጀምሮ ሀማስ በሰነዘረው ጥቃት 1400 ሰዎች መገደላቸውንና ከ3 ሸህ በላይ ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን እስራኤል ገልጻለች።
ከእስራኤል ጦር
ሃማስ ባሳለፍነው ሳምንት ጥቃት ከሰነዘረ ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ 291 የእስራኤል ወታደሮች መሞታቸውን የእስራኦል ጦር አስታውቋል።