እስራኤላውያን በጋዛ የሚካሄደው ጦርነት እንዲቀጥል ይፈልጋሉ ተባለ
በቅርብ ጊዜ የተሰበሰቡ የህዝብ አስተያየቶች ከ75 በመቶ በላይ እስራኤላውያን ጦርነቱ እንዲቀጥል ፍላጎት እንዳላቸው አመላክተዋል
ሃማስ በበኩሉ ከ100 በላይ ወታደሮች የተገደሉባት እስራኤል በጋዛ የምታሳካው ግብ የላትም ብሏል
እስራኤላውያን በጋዛ በንጹሃን ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት ከፍተኛ ቢሆንም ጦርነቱ መቀጠል እንዳለበት ይደግፋሉ ተባለ።
ከሁለት ወራት በላይ ባስቆጠረው ጦርነት ከ18 ሺህ 500 በላይ እስራኤላውያን እና ከ1 ሺህ 200 በላይ እስራኤላውያን ህይወት ተቀጥፏል።
በጦርነቱ የተገደሉ የእስራኤል ወታደሮች ቁጥርም 115 መድረሱ ነው የተነገረው።
ሬውተርስ ያነጋገራቸው እስራኤላውያን ግን ጦርነቱ ምንም እንኳን ሰብአዊ ውድመቱ ቀላል ባይሆንም ሃማስ እስኪወገድ ድረስ መቀጠሉ ተገቢ ነው ይላሉ።
እስራኤል የጥቅምት 7ቱን ጥቃት ያቀነባበሩ የሃማስ ታጣቂዎችን ካልደመሰሰች አልያም በቁጥጥር ስር ካላዋለች፤ ቀሪ ታጋቾችን ካላስለቀቀች ጦርነቱ መቀጠሉ ግድ መሆኑን በመጥቀስ።
የእስራኤል የዴሞክራሲ ኢንስቲትዩት በቅርቡ ከህዝብ ሰበሰብኩት ያለው አስተያየትም 75 በመቶ እስራኤላውያን ጦርነቱ መቀጠሉን እንደሚደግፉ አመላክቷል ተብሏል።
ጦርነቱ በርካታ የእስራኤል ወታደሮችን እንደሚቀጥፍ ቢታመንም እስራኤል በጠላትነት ከፈረጀቻቸው ሀገራት ሊቃጣባት የሚችል ጥቃትን ለመመከት ሃማስን ሙሉ በሙሉ ማጥፋት አለባት የሚለው የበርካቶቹ እምነት ነው ይላል ኢንስቲትዩቱ።
“ይህን ጦርነት ካላሸነፍን እንደ ኢራን ያሉ ሀገራት በሌላ ግንባር በሚያስታጥቋቸው አካላት ጦርነት ማወጃቸው አይቀርም” ባይ ናቸው ቤን ዚዮን ለቪንጀር የተባሉ እስራኤላዊ።
የቴል አቪቭ ዩኒቨርሲቲ የሰበሰበው የህዝብ አስተያየት የእስራኤል ጦር በጋዛ ያልተመጣጠነ እርምጃ እየወሰደ ነው ብለው የሚያምኑ እስራኤላውያን ከ10 በመቶ እንደማይበልጥ አመላክቷል።
የእስራኤል መገናኛ ብዙሃን በፍልስጤማውያን ላይ እየደረሰ የሚገኘውን ሰቆቃ እንደ አለማቀፍ ሚዲያዎች ሽፋን አይሰጡትም፤ የሚዘግቡትም ለጥቅምት 7ቱ ጥቃት እንደበቀል የተወሰደና በጦርነት ውስጥ ተጠባቂ ነገር እንደሆነ ቀለል አድርገው ያቀርቡታል።
ከህዝብ ተሰበሰቡ የተባሉት አስተያየቶች እስራኤላውያን ጦርነቱ እንዲቀጥል ፍላጎት አላቸው ቢሉም ቴል አቪቭ ሃማስን መደምሰስም ሆነ ታጋቾችን በፍጥነት ማስለቀቅ አልቻለችም።
ሃማስ በበኩሉ በትናንትናው እለት አንድ ኮሎኔልን ጨምሮ 10 የእስራኤል ወታደራቸውን በመጥቀስ ቴል አቪቭ በጋዛ የምታሳካው ግብ የላትም ብሏል።
የጦርነቱ እየተራዘመ መሄድም እስራኤልን ከባድ ዋጋ እንደሚያስከፍላት ገልጿል።