ጠቅላይ ሚኒስትሩ እስራኤል ክትባቱን ካገኙ ቀዳሚዎቹ ሃገራት መካከል አንዷ መሆኗን አስታውቀዋል
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከእስራኤላውያን ቀድመው ተከተቡ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሼባ በተሰኘ የህክምና ማዕከል ተገኝተው ነው በአሜሪካው ፋይዘር የተዘጋጀውን የኮሮና ክትባት በግል ዶክተራቸው አማካይነት የተከተቡት፡፡
ክትባቱ ቀሪውን ተከታቢ ለማበረታታት ይበጃል በሚል በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ሲተላለፍ ነበረ፡፡
የጤና ሚኒስትሩ ዩዲ ኤደልስቴይንም ተከትበዋል፡፡
ወደ ክትባቱ ሳመራ ወላጆቻቸውን ስለሚንከባከቡ ልጆች እና አያቶቻቸውን ማቀፍ ስለሚፈልጉ የልጅ ልጆች አሰብኩ ያሉት ኔታንያሁ ሃገራችንን እና ህይወታችንን ወደ ነበረበት መደበኛ ሁኔታ ለመመለስ የንግድ ባለቤቶች መንቀሳቀስ መቻል አለባቸው ሲሉ በይፋዊ የማህበረሰብ ገጾቻቸው ገልጸዋል፡፡
ለግለሰብ የምታንሰው ትንሿ ክትባት ለሁሉም ጤና መጠበቅ የምትበጅ ትልቅ እርምጃ እንደሆነችም ነው ያሰፈሩት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ክትባቶችን ትንሿ ሲሉ ወደጠሯት ወደ እስራኤል ለማምጣት በርትተው መስራታቸውን የገለጹ ሲሆን ክትባቱን ካገኙ ቀዳሚዎቹ ሃገራት መካከል ሃገራቸው አንዷ መሆኗን አስታውቀዋል፡፡
ይህ እንደ ቀላል እንደማይታይም ነው የገለጹት፡፡
ከመቼውም ጊዜ በላይ ተደስቻለሁም ብለዋል ኔታንያሁ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆናቸው በጣም መኩራታቸውን በመጠቆም፡፡
ጤና ሚኒስትሩ ኤደልስቴይንም የመጀመሪያዋን ክትባት የተከተቡባትን የትናንትናዋን ምሽት በሶቪዬት ሕብረት ከነበራቸው ቆይታ ጋር አገናኝተው ስሜት የተጫነው ንግግር አድርገዋል፡፡
ዕለቱ ከ36 ዓመታት በፊት ከሶቪዬት ሕብረት ወደ እስራኤል ለመመለስ በመፈለጋቸው ምክንያት ለህግ ከቀረቡበት ዕለት ጋር የሚገጣጠም ነበረ፡፡
እስራኤላውያን ፋዋሽነቱ የተረጋገጠውን ክትባት ያለምንም ጥርጣ እና ማንታት መከተብ እንዲጀምሩም ኤደልስቴይን አሳስበዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ሩቨን ሩቭሊን እና ተጠባባቂው ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒ ጋንዝ ዛሬ እንደሚከተቡ ይጠበቃል፡፡
ከአጠቃላዩ የሃገሪቱ ህዝብ 60 በመቶ ያህሉ እንደሚከተብም የጀሩሳሌም ፖስት ዘገባ አመልክቷል፡፡