የፌዴራል መንግስት የ2017 አጠቃላይ በጀት 1.5 ትሪሊየን ብር ደረሰ
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለ2017 በጀት ዓመት 582 ቢሊየን ብር ተጨማሪ በጀት አፀደቀ
ምክር ቤቱ በሰኔ ወር ላይ ለ2017 በጀት ዓመት 971.2 ቢሊየን ብር በጀት ማጽደቁ ይታወሳል
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለፌደራል መንግስት ለ2017 በጀት ዓመት ተጨማሪ በጀት የቀረበለትን 582 ቢሊየን ብር አጸደቀ።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው እለት ባካሄደው 6ኛ መደበኛ ስብሰባው ተጨማሪ በጀቱን ማጽደቁን ከምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
ተጨማሪ በጀት ለውጭ እና ለሀገር ውስጥ ዕዳ ክፍያ፣ ለማህበራዊ በጀት ድጎማ (ለማዳበሪያ፣ ለመድሐኒት፣ ለምግብ ዘይትና ሌሎች)፣ ለካፒታል ፕሮጀክቶች ማስፋፊያ፣ ለማህበራዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም እና ለመንግስት ሰራተኞች ደመወዝ ማሻሻያ እንደሚውልም የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) አብራተዋል።
በዚህም መሰረት ከቀረበው 582 ቢሊየን ብር ተጨማሪ በጀት ውስጥ ለመደበኛ ወጪ 393 ቢሊየን ብር፣ ለካፒታል ወጪ 70 ቢሊየን ብር፣ ለወጪ አሸፋፈን ማስተካከያ 119 ቢሊየን ብር መሆኑንም ተስፋዬ በልጅጌ ዶ/ር አስረድተዋል።
ምክር ቤቱ አባላትም ተጨማሪ በጀቱ አልበዛም ወይ? በገበያው ውስጥስ የዋጋ ግሽበትን አያስከትልም ወይ? ከተጨማሪ በጀት ውስጥ 282 ቢሊየን ብር ከግብር የሚሰበሰብ ከሆነ በግብር ከፋዮች ላይ ጫና አያሳድርም ወይ? የሚሉት ጥያቄዎችን አንስተዋል።
የገንዘብ ሚኒትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በሰጡት ምላሽ፤ የቀረበው ተጨማሪ በጀት 120 ሚሊየን ህዝብ ላላትና በኢኮኖሚ በማደግ ላይ ላለች ሀገር ብዙ የሚባል እንዳልሆነ ገልፀዋል።
ተጨማሪ በጀቱ ከሀገር ውስጥ እና ከውጪ ከሚገኝ ገቢ የሚሸፈንና ዝቅተኛ ተከፋይ ለሆኑ የመንግስት ሰራተኞች እንዲሁም ለሴፍቲኔት ተጠቃሚዎች የሚውል በመሆኑ በዋጋ ግሽበቱ ላይ ለውጥ እንደማያመጣም ክብሩ አቶ አህመድ ሺዴ አብራርተዋል፡፡
ምክር ቤቱ በቀረበው የፌደራል መንግስት 2017 በጀት ዓመት ተጨማሪ በጀት ረቂቅ አዋጅ ላይ ከተወያየ በኋላ በሶስት ተቃውሞ እና በአምስት ድምፀ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ አፅድቆታዋል።
ምክር ቤቱ በሰኔ ወር ላይ የ2017 በጀት ዓመት የፌደራል መንግስት መደበኛ በጀት ከዚህ ቀደም 971.2 ቢሊዮን ሆኖ ማጽደቁ የሚታወስ ሲሆን፤ ይህንን ተከትሎም የፌዴራል መንግስት የ2017 አጠቃላይ በጀት 1.5 ትሪሊየን ብር አድርሶታል።
በወቅቱ በቀረበው የ2017 በጀት ዓመት የፌደራል መንግስት መደበኛ በጀት ውስጥ 451 ቢሊዮን ብር ለመደበኛ ወጪ፣ 283.2 ቢሊዮን ብር ለካፒታል፣222.7 ቢሊዮን ብር ለክልል መንግሥታት ድጋፍ እንዲሁም ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ 140 ቢሊዮን ብር ተመድቧል።
ከ2017 በጀት 139.3 ቢሊዮን ብር ለዕዳ ክፍያ የመደበው መንግስት በበጀት አመቱ ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ጉዳዮች መካከል የዕዳ ክፍያ አንዱ ነው እንደሆነም በወቅቱ ተገልጿል።
መንግሥት የ2017 በጀት ለመሸፈን ከሀገር ውስጥ የገቢ ምንጮች፤ ከውጭ ዕርዳታ እና ብድር 612.7 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ማቀዱንም በወቅቱ አስታውቋል።