አስመራ የገቡት ጀነራል አልቡርሃን ከፕሬዝደንት ኢሳያስ ጋር "በጂኦፖለቲካዊ ጉዳዮች" ላይ እንደሚመክሩ ሚኒስትሩ ገለጹ
ጀነራል አልቡርሃን ወደ ኤርትራ ያቀኑት የባህልና ሚዲያ ሚኒስትሩን ካሊድ አል አሰር እና የደህንነት ኃላፊውን አውል አህመድ ኢብራሂም ሞፋዚልን አስከትሎ ነው
በሱዳን፣ ጀነራል አልቡርሃን እና ጀነራል ሀምዳን ደጋሎ ወይም ሄሜቲ በሚመሯቸው ጦሮች መካከል የተጀመረው ጦርነት 2 1/2 በላይ አመት አስቅጥሯል
የሱዳን ሉአላዊ የሽግግር ምክር ቤት ፕሬዝደንት እና የሱዳን ጦር መሪ ጀነራል አልቡርሃን በዛሬው እለት አስመራ መግባታቸውን የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል ገልጸዋል።
የማነ በኤክስ ገጻቸው እንደገለጹት መሪዎቹ በሱዳን ወቅታዊ ሁኔታ እንዲሁም የጋራ ጉዳዮች በሆኑ ቀጣናዊ እና ጂኦፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ ይመክራሉ።
ጀነራል አልቡርሃን ወደ ኤርትራ ያቀኑት የባህልና ሚዲያ ሚኒስትሩን ካሊድ አል አሰር እና የደህንነት ኃላፊውን አውል አህመድ ኢብራሂም ሞፋዚልን አስከትለው ነው።
ዛሬ ጠዋት የሱዳን ሉአላዊ የሽግግር ምክርቤቱ ጀነራሉ በሱዳን የእርስበርስ ጦርነት ከተጀመረ በኋላ ዋና መቀመጫ ካደረጓት ፖርት ሱዳን ሲሸኙ የሚያሳይ ምስል ለቆ ነበር።
በሱዳን፣ ጀነራል አልቡርሃን እና ጀነራል ሀምዳን ደጋሎ ወይም ሄሜቲ በሚመሯቸው ጦሮች መካከል የተጀመረው ጦርነት 2 1/2 በላይ አመት አስቅጥሯል።
ጀነራሎቹ ወደ ጦርነት የገቡት ከአልበሽር ውድቀት በኋላ የሱዳንን ሽግግር ይመራሉ ተብለው በተሾሙት ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ ላይ መፈንቀል መንግስት ካደረጉ በኋላ ነበር።
በጦርነቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸውን እና ከ10 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ደግሞ በሀገር ውስጥ አለያም ድንበር አቋርጠው ወደ ሌሎች ሀገራት መሰደዳቸውን አለምአቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) መግለጹ ይታወሳል።