የአለማችን በእድሜ ትልቁ ሰው በ112 ዓመታቸው ህይወታቸው አለፈ
ረጅም እና አጭር ጊዜ የመኖራችን ሚስጥር በእኛ እጅ ላይ አይደለም የሚል አባባል ነበራቸው
የእድሜ ባለጸጋው አዛውንት የሊቨርፑል እግር ኳስ ቡድን ቀንደኛ ደጋፊ እንደነበሩም ተሰምቷል
ሪታኒያዊው የአለማችን በእድሜ ትልቁ ሰው በ112 ዓመታቸው መሞታቸው ተዘግቧል፡፡
እ.ኤ.አ. ነሐሴ 26 ቀን 1912 የታይታኒክ መርከብ በሰመጠችበት በዚያው አመት የተወለዱት ቲኒስዉድ በ2020 በብሪታንያ በእድሜ ትልቁ ሰው በሚል ተመዝግበው የነበረ ሲሆን በ2024 ደግሞ በአለም ድንቃድንቅ መዝገብ በእድሜያቸው እውቅና አግኝተዋል።
በሁለተኛው የአለም ጦርነት በእንግሊዝ ሮያል አርሚ ውስጥ ተካተው ሀገራቸውን ያገለገሉት የእድሜ ባለጸጋው፤ አስተዋይ፣ ቆራጥ፣ ደፋር፣ በማንኛውም ችግር ውስጥ የተረጋጉ፣ ፈጣን የሂሳብ ችሎታ ያላቸው እና ተግባቢ እንደነበሩ ቤተሰቦቻቸው ይናገራሉ፡፡
በ1942 ከባለቤታቸው ቦልድዊን ጋር ትዳር መስርተው አንድ ሴት ልጅ የወለዱ ሲሆን በእድሚያቸው 4 የልጅ ልጅ እና 3 የልጅ ልጅ ልጆችን አይተዋል፡፡
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቃት በኋላ በሮያል ሜይል እና በኋላም የሼል እና ቢፒ ኩባንያዎች የሂሳብ ሰራተኛ በመሆን ጡረታ እስከወጡበት 1972 ድረስ አገልግለዋል።
አዛውንቱ ቲኒስዉድ ከመሞታቸው በፊት ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቃለ መጠይቅ በወጣትነታቸው ንቁ እና ብዙ የእግር ጉዞዎችን የሚያዘወትሩ ሰው እንደነበሩ ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም “ረጅም እና አጭር ጊዜ የመኖራችን ሚስጥር በእኛ እጅ ላይ አይደለም ለምን በዚህ ልክ በረጅም እድሜ እንደተባረኩ አላውቅም” ብለው ነበር፡፡
እርሳቸው ከመወለዳቸው 20 አመታት ቀደም ብሎ የተመሰረተው የሊቨርፑል እግር ኳስ ቡድን ቀንደኛ ደጋፊ እንደነበሩ የሚነገርላቸው የእድሜ ባለጸጋው የቡድኑን በርካታ ጨዋታዎች በስታድየሞች በመገኝት ይታደሙ እንደነበርም ተገልጿል፡፡
እ.ኤ.አ. በ 2012 100 ኛ አመት የልደት በአላቸውን ካከበሩበት ጊዜ ጀምሮ ከእንግሊዝ ንግስት ኤልዛቤት ሁለተኛ በየአመቱ የመልካም ምኞት መግለጫ የልደት ካርድ ይላክላቸው የነበረ ሲሆን ይህን ሂደት አዲሱ ንጉስ ቻርልስ ሶስተኛም አስቀጥለውት ነበር ሲል ቢቢሲ አስነብቧል፡፡