የተመዘበረው ገንዘብ ከአምናው ጋር ሲነጻጸር በ300 ሚሊዮን ብር ጭማሪ አሳይቷል ተብሏል
የኢትዮጵያ ባንኮች 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር መጭበርበራቸው ተገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዓመታዊ የገንዘብ ደህንነት ሪፖርቱን ይፋ አድርጓል፡፡ የባንኩ ሪፖርት እስከ ሰኔ 2024 ድረስ ያሉ የገንዘብ እንቅስቀሴዎች ዙሪያ ትኩረቱን አድርጓል፡፡
ባንኩ በሪፖርቱ ላይ እንደጠቀሰው 28 የኢትዮጵያ ባንኮች 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በአጭበርባሪዎች ገንዘባቸውን አጥተዋል ብሏል፡፡
የማጭበርበር ድርጊቶቹ የተፈጸሙት በሐሰተኛ የገንዘብ ኖቶች፣ በተሰረቁ የኤትኤም ማሽኖች፣ በሐሰተኛ ቼኮች፣ በሐሰተኛ የስልክ መልዕክት እና ተያያዥ መንገዶች አማካኝነት ነው፡፡
በዚህ ዓመት ባንኮች ያጡት ገንዘብ ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ300 ሚሊዮን ብር ጭማሪ እንዳሳየም በሪፖርቱ ላይ ተጠቅሷል፡፡
በኢትዮጵያ በአጠቃላይ ካሉ 31 ባንኮች ውስጥ 28ቱ ሲጭበረበሩ የቀሪዎቹ ሶስት ባንኮች ማንነት ግን በሪፖርቱ ላይ አልተጠቀሰም፡፡
ባንኮች ከአነስተኛ የብድር እና ቁጠባ ተቋማት ጋር በመቀናጀት ብድሮችን እየሰጡ ነው የተባለ ሲሆን ይህ አገልግሎት እየጨመረ መሄድ እና የበይነ መረብ ማጭበርበሮች መበራከት ባንኮች የሚያጡት ገንዘብ ሊጨምር እንደሚችል ብሔራዊ ባንክ በሪፖርቱ ላይ ጠቅሷል፡፡
ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን የ738.2 ሚሊየን ዶላር ብድር ሰጠች
ብሔራዊ ባንክ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የገንዘብ እንቅስቃሴ ጤናማ ደረጃ ላይ ይገኛሉ ያለ ሲሆን እስከ ሰኔ 2024 ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ 2 ነጥብ 5 ትሪሊዮን ብር በባንኮች ውስጥ ሲቆጠብ የተሰጠ ብድር መጠን ደግሞ 2 ነጥብ 2 ትሪሊዮን ብር እንደደረሰም ገልጿል፡፡
የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ 345 ቢሊዮን ብር፣ የሀገር ውስጥ ንግድ 302 ቢሊዮን ብር እንዲሁም የወጪ ንግድ ዘርፍ ደግሞ 212 ቢሊዮን ብር ብድር ተሰጥቷቸዋል ተብሏል፡፡
ይሁንና የግብርና ስራዎች ዝቅተኛ የገንዘብ መጠን በብድር መልክ ያገኘ ሲሆን ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ ምርቶች ለማስገባት እና ሌሎች የንግድ ዘርፎችም በቅደም ተከትል አነስተኛ የብድር አቅርቦት ያገኙ ዘርች ሆነዋል፡፡
የባንኮች አጠቃላይ ትርፍም ባለፈው ዓመት ከነበረበት 49 ቢሊዮን ብር ወደ 59 ቢሊዮን ብር ከፍ ማለቱም ተገልጿል፡፡