
የታጋቾችና እስረኛ ልውውጡ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ላይ ያንዣበበውን የመፍረስ ስጋት ቀንሷል
ከሳምንታት በፊት የተደረሰውን የተኩስ አቁም ስምምነት ተከትሎ ሀማስ 3 ታጋቾችን ሲለቅ፣ እስራኤል ደግሞ 369 ፍልስጤማውያን ከእስር መልቀቋ ተገለጸ።
ሃማስ በዛሬው እለት በካንዩኒስ የለቀቃቸው ሶስት እስራኤላውያን ታጋቾች ኢየር ሆርን፣ ሳጊ ዴከል-ቼን እና ሳሻ (አሌክሳንደር) ትሮፋኖቭ መሆናው ታውቋል።
በምትኩም እስራኤል በእስር ቤቶቿ ውስጥ የነበሩ 369 ፍሊስጤማውያንን መልቀቅ መጀመሯ ነው የተነገረው።
ሶስቱ ታጋቾች በእስራኤል ጦር ወደ ሀገራው ከመወሰዳቸው በፊት ከጋዛ ካን ዩኒስ ሲለቀቁ የሚያሳይ ምስል በቀጥታ ተላልፎ ነበር።
ብዙም ሳይቆይ ነፃ የወጡ የፍልስጤም እስረኞችን የጫነ የመጀመሪያው አውቶቡስ ከእስራኤል ኦፈር እስር ቤት ሲወጣ የሚያሳይ ምስልም በቀጥታ ስርጭት ታይቷል።
ከእስራኤል እስር ቤት የተለቀቁት ፍልስጤማውያን እስረኞች ያሳፈረው ባስ በዌስትባንክ ራማላህ ሲገባ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አቀባበል አድርገዋል።
በቴልአቪቭ የታጋቾች አደባባይ ተብሎ የሚጠራ ስፍራ ላይ የነበሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ እስራኤላውያንም 3ቱን ታጋቾች ቀይ መስቀል ከሃማስ ተቀብሎ ለእስራኤል ጦር ማስረከቡን እንደሰሙ ደስታቸውን ሲገልጹ ታይተዋል።
የሶስቱ እስራኤላውያን ታጋቾች እና 369 ፍልስጤማውያን እስረኞች ልውውጥ በዛሬው እለት መካሄዱ በፈረንጆቹ ጥር 19 የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ሊፈርስ ይችላል በሚል ተደቅኖ የነበረው ስጋት ቀንሷል።
በእስራኤል እና በሃማስ መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት ከተደረሰ ወዲህ እስካሁን ሃማስ 19 እስራኤላውያንና 5 የታይላንድ ታጋቾች ሲለቅ እስራኤል በመቶዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ከእስር ለቃለች።
73 እስራኤላውያን አሁንም በሃማስ እገታ ስር የሚገኙ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል ግማሽ ያህሉ ሳይሞቱ እንዳቀረ የእስራኤል ባለስልጣናት አስታውቀዋል።