እስራኤል በሰሜናዊ ጋዛ በ48 ስአት ውስጥ ከ50 በላይ ህጻናትን መግደሏን ዩኒሴፍ ገለጸ
የፖሊዮ ክትባት በመውሰድ ላይ በነበሩ ህጻናት ላይ ቦምብ መጣሏም አለማቀፉን የሰብአዊነት ህግ የጣሰ ነው ብሏል
በእስራኤል ጥቃት የተገደሉ ፍልስጤማውያን ህጻናት ቁጥር ከ18 ሺህ በላይ መድረሱ ተገልጿል
እስራኤል በሰሜናዊ ጋዛ በ48 ስአት ውስጥ ከ50 በላይ ህጻናትን መግደሏን ዩኒሴፍ ገለጸ።
የመንግስታቱ ድርጅት የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ትናንት በድረገጹ ባወጣው መግለጫ በጃባሊያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የተጠለሉባቸው ሁለት ህንጻዎች በእስራኤል ጥቃት መፈራረሳቸውን ጠቁሟል።
በሼክ ራድዋን ሆስፒታል ውስጥ የፖሊዮ ክትባት በመውሰድ ላይ በሚገኙ ህጻናት ላይ ቦምብ በመጣሏም በጥቂቱ ሶስት ህጻናት መቁሰላቸውን ነው መግለጫው የጠቆመው።
“ከጃባሊያ ወደ ኢልናዝላ ስታሽከርክር የነበረች የዩኒሴፍ ሰራተኛ ጥቃት ተሰንዝሮባት ተሽከርካሪዋ ተጎድታለች” ያለው ተቋሙ፥ ሶስቱም ጥቅቶች በጋዛ እየተፈጸመ የሚገኘው “የጅምላ ጥቃት” ማሳያ መሆናቸውን አብራርቷል።
አንድ አመት ባለፈው የእስራኤል እና ሃማስ ጦርነት ከተገደሉ ከ43 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን ውስጥ ከ18 ሺህ በላዩ ህጻናት መሆናቸው ተገልጿል።
በሴቶችና ህጻናት ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት “የጋዛው ጦርነት ጥቁር ምዕራፍ ነው” ያለው የመንግስታቱ ድርጅት የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ)፥ ንጹሃን እና የንጹሃን መኖሪያዎች፣ የሰብአዊ ድርጅቶች ሰራተኞች እና ተሽከርካሪዎች ከጥቃት መጠበቅ እንደሚገባቸው ገልጿል።
ይሁን እንጂ እስራኤል ህጻናት እና የንጹሃን መኖሪያዎችን በመደብደብ ከአለማቀፉ ህግ በተቃርኖ መቆሟን ቀጥላለች ነው ያለው ተቋሙ ባወጣው መግለጫ።
ዩኒሴፍ እስራኤል በተቋሙ ሰራተኞች ላይ እየተፈጸሙ የሚገኙ ጥቃቶችን በመመርመር ጥፋተኞችን ተጠያቂ እንድታደርግም አሳስቧል።
ፍልስጤማውያን ህጻናት ከጦርነቱ ባሻገር በረሃብ እና በበሽታዎች ህይወታቸው አደጋ ላይ ባለበት ወቅት የሚፈጸሙ ድብደባዎች መቀጠል እጅግ አሳሳቢ መሆኑንም ነው የጠቆመው።
እስራኤል በጋዛ “ሃማስን ሙሉ በሙሉ ለመደምሰስ” ጀመርኩት ያለችው ጦርነት ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰው በህጻናትና ሴቶች ላይ ነው።
የአለም ጤና ድርጅት እና የመንግስታቱ ድርጅት ተቋማት የኔታንያሁ አስተዳደር የጥቃት ኢላማዎቹ ላይ ጥንቃቄ እንዲያደርግ በተደጋጋሚ ቢያሳስቡም የንጹሃኑ እልቂት ቀጥሏል።