የእስራኤል ወታደራዊ መሪዎች በጋዛ እና በሊባኖስ ስራቸውን መጠናቀቁን አመለከቱ
መሪዎቹ በወታደራዊ ዘመቻ ሀገሪቱ ማሳካት የሚጠበቅባትን በሙሉ ስላሳካች ፖለቲካዊ መፍትሄ ላይ ትኩረት እንዲደረግ እየጠየቁ ነው
አሁን ጥያቄው ጠቅላይ ሚንስትር ኔታንያሁ ይህን ሀሳብ ይቀበሉ ይሆን? የሚል ሆኗል
የእስራኤል ወታደራዊ መሪዎች ሀገሪቱ በጋዛ እና ሊባኖስ በወታደራዊ ዘመቻዎች ማከናወን የፈለገቻቸውን አላማዎች በሙሉ ማሳካቷን አመልከተዋል፡፡
ሲኤንኤን እንደዘገበው መሪዎቹ በይፋ ባይሆንም ወታደራዊ ዘመቻዎቹ መጠናቀቃቸውን እና ጦሩ ከዚህ በኋላ በሁለቱ ስፍራ መቆየቱ እምብዛም ጥቅም እንደሌለው እየተናገሩ እንደሚገኝ ዘግቧል፡፡
በወታደራዊ ኃይል የምትችለውን ሁሉ እንዳሳካች የገለጹት አዛዦቹ ፖለቲከኞች ስምምነት ላይ ለመድረስ ጊዜው አሁን መሆኑን አመላክተዋል፡፡
የእስራኤል ጦር ከፍተኛ ጄነራል ከሰሞኑ በሰሜናዊ ጋዛ ከሚገኙ መኮንኖች ጋር ወቅታዊ የጦርነቱን ሁኔታ ለመገምገም በነበራቸው ስብሰባ፤ የግጭቱ ከዚህ በኋላ መቆየት እምብዛም ጥቅም የለውም ማለታቸው ነው የተሰማው፡፡
የሀገሪቱ ኢታማዦር ሹም ሄርዚ ሄልቪ በበኩላቸው “በጋዛ የሰሜን ጋዛ ብርጌድ አዛዥን ብንገድል ለቡድኑ ሌላ ውድቀት ነው፤ ነገ ምን እንደሚገጥመን አላውቅም። ነገር ግን ይህ ጫና ወደ ተጨማሪ ስኬቶች እንድንቀርብ ያደርገናል” ብለዋል፡፡
በሊባኖስ ሄዝቦላህ ላይ እየተካሄደ በሚገኝው ጦርነት አሁን በሚገኝበት ደረጃ አንድ መደምደሚያ ላይ ለመድረስ እድሉ አለ ነው ያሉት ኢታማዦር ሹሙ፡፡
ከዚህ በፊት የእስራኤል የቀድሞ ጄነራሎች በተመሳሳይ የሀማሱ መሪ ያህያ ሲንዋር ግድያን የጋዛን ጦርነት ለማስቆም የኔታንያሁ አስተዳደር እንዲጠቀምበት መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡
በተጨማሪም ሁለቱም የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ዕጩዎች ስልጣን ሲይዙ የጋዛ እና የሊባኖስ ጦርነት ጉዳይ አጀንዳ እንዲሆን እንደማይፈልጉ እና ግጭቱ በቶሎ መቋጨት እንዳለበት በግልጽ አቋማቸውን ይፋ አደርገዋል፡፡
አሁን ጥያቄው ጠቅላይ ሚንስትር ኔታንያሁ ከጦር መሪዎቻቸው እና ከተለያዩ የፖለቲካ ሀይሎች እንዲሁም የውጭ አጋሮቻቸው ጦርነቱን እንዲያቆሙ እና ተጋቾችን ማስመለስ ላይ እውነተኛ ድርድር እንዲያደርጉ የቀረበላቸውን ጥሪ ይቀበሉ ይሆን የሚል ሆኗል፡፡
በጋዛ “ፍፁም ድል” ለማስመዝገብ ደጋግመው ቃል የገቡት ጠቅላይ ሚንስትር ኔታንያሁ ይህን ሀሳብ ለመቀበል የሚችገሩ ይመስላል፡፡
የመከላከያ ሚንስትራቸው ዮአቭ ጋላንት በነሀሴ ወር ከፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ ጋር በዝግ በተደረገ ስብሰባ “በጋዛ ፍፁም ድል የሚለው ሀሳብ ከንቱ ነው” ሲሉ መናገራቸው ተሰምቷል፡፡
ሚንስትሩ ከሰሞኑ ለጠቅላይ ሚንስትሩ ወቅታዊ ሁኔታዎችን አስመልክቶ ባቀረቡት ሪፖርትም “የተሻሻሉ የዘመቻ ግቦች በሌሉበት ባልጠራ ኮምፓስ እያደረግን ያለነው ውግያ የዘመቻውን ውጤት ይጎዳል” ማለታቸውን የእስራኤሉ ቻናል 13 መዘገቡን ሲኤንኤን ጠቅሷል፡፡
በተጨማሪም አሁን ላይ ትኩረት መደረግ የሚገባው በጋዛ የቀሩትን ታጋቾች ማስለቀቅ፣ ከሃማስ ምንም አይነት ወታደራዊ ስጋት አለመኖሩን ማረጋገጥ እና የሲቪል አገዛዝን ተግባራዊ ማድረግ ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል።