እስራኤል የጋዛ ከተማ አስተዳዳሪን ገደለች
ኔታንያሁ በጋዛ የሚደረስ የተኩስ አቁም ስምምነት እስራኤል ግቧን እስክትመታ ድረስ ጦርነቱ እንዲቀጥል መፍቀድ አለበት ብለዋል
ሃማስ በአዲሱ የተኩስ አቁም ምክረሃሳብ ዙሪያ የእስራኤልን ምላሽ እየጠበቀ ነው
እስራኤል በጋዛ በፈፀመችው የአየር ጥቃት ከፍተኛ የሃማስ ሀላፊ ተገደሉ።
ኢሃብ አል ሁሴን የተባሉት የጋዛ ከተማ አስተዳዳሪ እስራኤል"ሆሊ ፋሚሊ" በተሰኘ ትምህርት በፈፀመችው ጥቃት ከተገደሉት አራት ሰዎች መካከል አንዱ ናቸው ተብሏል።
አል ሁሴን የጋዛ ከተማ እና ሰሜናዊ ጋዛን እንዲያስተዳድሩ የተሾሙት ከሶስት ወራት በፊት ነበር።
የእስራኤል ጦር በትምህርት ቤቱ ላይ ጥቃቱን የፈፀመው "ሽብርተኞች" ተደብቀው እያሴሩበት ነው በሚል ነው።
የአይን እማኝች ግን ትምህርት ቤቱ በርካታ ንፁሃን የተጠለሉበት መሆኑን ነው ለቢቢሲ የገለፁት።
የቀድሞው ምክትል የሰራተኞች ሚኒስትር ኢሀብ አል ሁሴን ግድያ በሃማስ ወታደራዊ እንቅስቃሴ ላይ የጎላ ተፅዕኖ ይኖረዋል ተብሎ አይጠበቅም።
ዘጠኝ ወራት ባስቆጠረው የጋዛ ጦርነት እስራኤል በርካታ የሃማስ አመራሮችን መግደሏ ይታወቃል።
አመራሮቹ ላይ ኢላማ ያደረጉት ጥቃቶች የበርካታ ንፁሀንን ህይወት ቀጥፈው ጋዛን ማፈራረሳቸውም ይነገራል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በጋዛ የሚደረስ የተኩስ አቁም ስምምነት እስራኤል ግቧን እስክትመታ ድረስ ጦርነቱ እንዲቀጥል መፍቀድ አለበት የሚል አስተያየት መስጠታቸውም የፍልስጤማውያን ሰቆቃ ቀጣይነትን አመላክቷል።
የኔታንያሁ አስተያየት በኳታር ባለፈው ሳምንት በተጀመረውና በዚህ ሳምንትም ይቀጥላል በተባለው ድርድር ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳርፍ ተገምቷል።
አሜሪካ ያቀረበችውን በስድስት ምዕራፍ የተከፋፈለ የተኩስ አቁም ስምምነት መቀበሉን ያስታወቀው ሃማስ በበኩሉ የእስራኤልን ምላሽ እየተጠባበቀ መሆኑን ገልጿል።
አሜሪካ ከ38 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያንን ህይወት የቀጠፈው ጦርነት በህዳር ወር ከምታካሂደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በፊት እንዲቆም ግፊት እያደረገች ነው ቢባልም ከቴል አቪቭ የሚሰማው ጦርነቱ መቀጠል አለበት የሚል ብቻ ሆኗል።