የጠቅላይ ሚንስትር ኔታንያሁን አስተዳደር የሚቃወሙ እስራኤላውያን ለተቃውሞ አደባባይ ወጥተዋል
ሰልፈኞቹ መንግስት እንዲበተን እና አዲስ ምርጫ እንዲደረግ በመጠየቅ ላይ ናቸው
የአስቸኳይ ጊዜ መንግስታቸውን የበተኑት ኔታንያሁ በሰሜን የሀገሪቱ ድንበር ከሂዝቦላ ጋር የሚገኙበት ውጥረት ተባብሷል
በሺዎች የሚቆጠሩ እስራኤላዊያን የኔታንያሁን መንግሰት መፍረስ በአደባባይ በመጠየቅ ላይ ናቸው፡፡
ትላንት እና ዛሬ በቀጠለው የተቃውሞ ሰልፍ ተቃዋሚዎቹ ወደ ፓርላማው እና ወደ ጠቅላይ ሚንስትሩ መኖርያ ቤት በማቅናት ተቃውሟቸውን እየገለጹ ነው፡፡
ወትሮም ቢሆን በተለያየ ርዕዮት ውስጥ በሚገኙ ፓርቲዎች የተዋቀረው የእስራኤል መንግስት ስንጥቃት እየሰፋ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚንስትሩ የጋዛውን ጦርነት በመሩበት ሂደት ተቃውሞ ያላቸው ፓርቲዎች በኔታንያሁ ላይ በጓሮ እና በፊት ለፊት ተቃውሟቸውን እያሰሙ ነው፡፡
የአስቸኳይ መንግስቱ አባል የሆኑት ቤኒ ጋንቴዝ ከአባልነታቸው በገዛ ፍቃዳቸው ከተነሱ በኋላ በኔታንያሁ አስተዳደደር ላይ ከፖለቲካው ሀይል እና ከዜጎች የሚነሳው ተቃውሞ ጠንክሯል፡፡
ተቃዋሚ ፓርቲዎች በእየሩሳሌም ለሳምንት እንዲዘልቅ በጠሩት ሰላማዊ ሰልፍ ዋና ዋና መንገዶች እንዲዘጉ የተቃውሞ ሰልፎች እንዲቀጥሉ አዘዋል፡፡
ትላንት አመሻሹን ወደ ኔታንያሁ የግል መኖርያ ቤት ያቀኑት ሰልፈኞች የፖሊስ አጥርን ሰብረው ወደ መኖርያ ቤቱ ለመጠጋት ሲሞክሩ ከፖሊስ ጋር ተጋጭተዋል ፖሊስ ተቃዋሚዎችን በውሀ ለመበተን ጥረት ያደረገ ሲሆን እስካሁን 9 ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
ሮይተርስ እንደዘገበው ተቃዋሚዎቹ “ኔታንያሁ ታጋቾቹ የታሉ”፣ “በሃማስ እና በሂዝቦላ ተሸንፍሀል ከስልጣን ልቀቅ” የሚሉ መፈክሮችን ይዘው ታይተዋል፡፡
ተቃውሞውን ተከትሎ ጠቅላይ ሚንስተሩ ከመከላከያ ሚንስትሩ ዮቭ ጋላንት እና ከስትራቴጂካዊ ጉዳይ ሚንስትሩ ሮን ደርመርን ጨምሮ ከሌሎች ሚንስትሮቻቸው ጋር በጋዛ ጦርነት ቀጣይ ሁኔታ እና በሰሜን የሀገሪቱ ድንበር በኩል ውጥረትን ስለፈጠረው ሂዝቦላ ጉዳይ ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በኢራን ከሚደገፈው ሂዝቦላ ጋር እስራኤልን ከሊባኖስ ጋር በሚያዋስናት ድንበር ላይ ያለው ውጥረት ከሰሞኑ ከፍ ብሎ ታይቷል፡፡ ሰማያዊ መስመር ተብሎ በሚጠራው የሊባኖስ የእስራኤል ዜጎች ከሚኖርበት ስፍራ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አካባቢውን እንዲለቁ ተደርገዋል፡፡
በጋዛ በምዕራብ ራፋ ቴል ሱልጣን እና በማዕከላዊ ጋዛ የእስራኤል ጦር ከሀማስ ጋር የሚያደርገው ውጊያ አሁንም ቀጥሏል፡፡
ከፖለቲካዊ ሀይሎች፣ ከአለም አቀፉ ማህበረሰብ እና ከዜጎቹ ጫና የበረታበት የኔታንያሁ መንግስት ይህን ፖለቲካዊ ምስቅልቅል ለማለፍ የአሜሪካን የተኩስ አቁም ስምምነት ሀሳብ መቀበል አልያም መንግስቱን በትኖ ወደ ምርጫ ሊገባ እንደሚችል ይጠበቃል፡፡