እስራኤል በዌስትባንክ ከ800 ሄክታር በላይ መሬት ነጥቃ ከለለች
ቴል አቪቭ የመንግስት ይዞታ ነው ብላ ባወጀችው መሬት ላይ የሰፈራ ቤቶች እና የንግድ ተቋማትን ትገነባለች ተብሏል
እስራኤል በቅርቡ በዌስትባንክ 3 ሺህ 400 ቤቶችን ለመገንባት የወጣውን እቅድ ማጽደቋ ይታወሳል
እስራኤል በሀይል በያዘችው ዌስትባንክ ከ800 ሄክታር በላይ መሬት ነጥቃ መከለሏ ተነገረ።
በ10 አመት ውስጥ ከፍልስጤም ከፍተኛው የመሬት ዝርፊያ ነው የተባለለትን ድርጊት የመብት ተሟጋቾች እየተቃወሙት ነው።
የእስራኤል የፋይናንስ ሚኒስትር ባዛሌል ስሞትሪች፥ በሰሜናዊ ዮርዳኖስ ሸለቆ የሚገኘው መሬት በእስራኤል መንግስት ባለቤትነት እንዲተዳደር መወሰኑ “ወሳኝና ስትራቴጂካዊ ነው” ብለዋል።
ውሳኔው በስፍራው የሰፈራ ቤቶችን እና የንግድ ህንጻዎችን ለመገንባት የሚያስችል መሆኑን መግለጻቸውንም ታይምስ ኦፍ እስራኤል አስነብቧል።
እስራኤል በሃይል በያዘችው የፍልስጤም መሬት ላይ የምታከናውነው የሰፈራ ፕሮግራም በአለማቀፉ ህግ ተቀባይነት የለውም።
የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክርቤትም በ2016 ባወጣው መግለጫ የእስራኤል የሰፈራ ፕሮግራም የእስራኤልና ፍልስጤም ግጭትን ለመቋጨት ይረዳል የተባለውን የሁለት መንግስታት መፍትሄ ወይም “ቱ ስቴት ሶሊዩሽን” ተግባራዊ ለማድረግ “እንቅፋት” ነው በሚል መቃወሙ ይታወሳል።
በዌስትባንክ እና ምስራቅ እየሩሳሌም የሚካሄዱ የሰፈራ ቤቶች ግንባታን የሚቃወመው የእስራኤሉ “ፒስ ናው”፥ እስራኤል በዌስትባንክ ከፍልስጤማውያን ነጥቃ የከለለችው መሬት ከ1993ቱ የኦስሎ ስምምነት በኋላ ሰፊው መሆኑን ጠቅሷል።
እስራኤል በ2024 በሃይል በያዘቻቸው የፍልስጤም መሬቶች ላይ የምታካሂደው ግንባታና ወረራ ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍተኛ መሆኑን በመጥቀስም ውሳኔውን ተቃውሟል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ አስተዳደር በዌስትባንክ እና ምስራቅ እየሩሳሌም 3 ሺህ 400 የሰፈራ ቤቶች እንዲገነቡ የወጣውን እቅድ በዚህ ወር መግቢያ ማጽደቁ ይታወሳል።
ይህም የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ኔታንያሁ እንደሚሉት ሃማስን የመደምሰስ ሳይሆን የፍልስጤም መሬትን የመቀራመት የረጅም ጊዜ እቅድ ማስፈጸሚያ ነው የሚለውን ትችት አጠናክሯል።
የመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቮልከር ቱርክም የእስራኤል የፍልስጤም መሬት ወረራ በዌስትባንክ ያለውን ውጥረት ይበልጥ ቀውስ ውስጥ የሚከት መሆኑን ነው ለጸጥታው ምክርቤት ባቀረቡት ሪፖርት ያመላከቱት።
የእስራኤሉ የፋይናንስ ሚኒስትር ባዛሌል ስሞትሪች በበኩላቸው የሰፈራ ፕሮግራሙ እስራኤል በታጣቂዎች የሚደርስባትን ጥቃት ለመመከት ወሳኝ ድርሻ አለው በማለት የሚነሱ ተቃውሞዎችን አጣጥለዋል።
እስራኤል በ1967ቱ የስድስት ቀናት ጦርነት በሃይል በተቆጣጠረቻቸው የፍልስጤም የቀድሞ ግዛቶች ዌስት ባንክ እና ምስራቅ ኢየሩሳሌም ቤቶች ገንብታ 700 ሺህ አይሁዳውያንን ማስፈሯ ይታወቃል።