ትራምፕ ሲቢኤስ ቴሌቪዥን ላይ የ10 ቢሊየን ዶላር ክስ መሰረቱ
የአሜሪካው የቴሌቪዥን ጣቢያ ለካማላ ሃሪስ የወገነና መራጮች ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር ዜና ሰርቷል በሚል ነው ክሱን የመሰረቱት
የ2024ቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ሊካሄድ አራት ቀናት ቀርተውታል
የአሜሪካ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሲቢኤስ ቴሌቪዥን ላይ የ10 ቢሊየን ዶላር ክስ መሰረቱ።
ትራምፕ ክሱን የመሰረቱት የቴሌቪዥን ጣቢያው ከምክትል ፕሬዝዳንት እና የምርጫ ተፎካካሪያቸው ካማላ ሃሪስ ጋር ያደረገውን ቆይታ ሃሪስን በሚያጎላ መልኩ የአርትኦት ስራ ሰርቶ አቅርቧል በሚል ነው።
በቴክሳስ ኖርዘርን ዲስትሪክት የቀረበው ክስ ሲቢኤስ በ”60 ደቂቃ” የዜና ፕሮግራሙ ላይ የሰራው አርትኦት ሃሪስን ባልተገባ መንገድ ከፍ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ጠቅሷል።
የቴሌቪዥን ጣቢያው “የፓርቲ አቋም አሳይቷል፤ በምርጫ ወቅት ሊፈጸም የማይገባ ህገወጥ ድርጊት ፈጽሟል፤ የተሳሳተ እና የሚያምታታው የአርትኦት ስራ በመራጮች ላይ ያልተገባ ተጽዕኖ ለማሳደር ያለመ” መሆኑንም ነው የጠቆመው።
ሃሪስ በጥቅምት ወር ከሲቢኤስ “60 ደቂቃ” ጋር ቆይታ ስታደርግ ከዚያ በፊት ስለ እስራኤልና ፍልስጤም ግጭት የሰጠችው ዘለግ ያለ ምላሽ በአርትኦት መካተቱ የቴሌቪዥን ጣቢያው “ሆን ብሎ ሃሪስን ለመደገፍና ትራምፕን ኢፍትሃዊ ባልሆነ ለመጉዳት” የተደረገ መሆኑንም ክሱ አብራርቷል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጠበቆች “ሃሳባቸውን በደንብ መግለጽ ለማይችሉት ሃሪስ ሲቢኤስ በአርትኦት ድጋፍ ሊሰጥ ሞክሯል” ሲሉ መናገራቸው አናዶሉ አስነብቧል።
ሲቢኤስ ኒው በትናንትናው እለት ለቀረበበት ክስ ፈጣን ምላሽ ሰጥቷል፤ የቴሌቪዥን ጣቢያው የትራምፕ ክስ “ከእውቀት (የዜና አሰራር) ውጭ መሆናቸውን ያሳያል” ብሏል።
“ከሃሪስ ጋር የተደረገው ቃለምልልስ ለተለየ አላማ የአርትኦት ስራ አልተከናወነበትም፤ “በ60 ደቂቃ” የዜና ፕሮግራሙ ላይ ምክትል ፕሬዝዳንቷ ለተነሱላቸው ጥያቄዎች የሰጡት ምላሽ ተመልካቾቻችን በሚሸውድ መልኩ ተቆርጦ አልተስተካከለም” ሲልም ክሱን ተከላክሏል።
የብሮድካስት ዜናዎች በአጭር ደቂቃዎች የተገደቡ ከመሆናቸው አንጻር ጥያቄዎችና ምላሾች ሊመጠኑ እንደሚችሉ በመጥቀስም ሙሉ ቃለምልልሱን በዜና ስአት ማቅረብ እንደማይቻል አብራርቷል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ለሃሪስ እያዳላ ነው ባሉት የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ እንዲቀርቡ ተመሳሳይ ጥያቄ ቀርቦላቸው ተስማምተው ነበር።
ይሁን እንጂ ሲቢኤስ ትራምፕ የሚሰጡትን ምላሽ ትክክለኛነት በመረጃ ማጣሪያ እንደሚያረጋግጥ ሲያሳውቅ ሃሳባቸውን መቀየራቸው ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
ዶናልድ ትራምፕ በመገናኛ ብዙሃን ላይ ክስ ሲመሰርቱ ሲቢኤስ የመጀመሪያው አይደለም።
ከዚህ ቀደም በሲኤንኤን፣ ዋሽንግተንፖስት፣ ኒውዮርክ ታይምስ እና ኤቢሲ ኒውስ ላይ የስማ ማጥፋት ዘመቻ ተከፍቶብኛል የሚሉና ከኢፍትሃዊነት ጋር የተያያዙ ክሶችን ማቅረባቸው አይዘነጋም።
ትራምፕ ዳግም ወደ ዋይትሃውስ ለመዝለቅ ከዴሞክራቷ ካማላ ሃሪስ ጋር የተናነቁበት የ2024ቱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ሊካሄድ አራት ቀናት ቀርተውታል።