ጥቃቱን ፈጽማለች የተባለችው ግለሰብ ፍቅረኛዋን ከመግደሏ በፊት መንገድ ላይ ሰላምታ በሰጠችው ሴት ላይ ጉዳት አድርሳለች
በፍቅር ውስጥ የሚኖር ትንሽ ቅናት የፍቅር ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ቢችልም ሲበዛ ለሞት እንደሚዳርግ በአርጄንቲና የተፈጠረው አሳዛኝ ክስተት አሳይቷል።
ማሪያኖ ግሪንሰፐን የተባለው የ23 አመት ወጣት አርጄንቲናዊ ለሌላ ሴት ሰላምታ ለምን ሰጠህ በሚል ቅናት በተነሳሳች ፍቅረኛው በስለት ተወግቶ ህይወቱ ማለፉ ተሰምቷል፡፡
አስደንጋጩ አጋጣሚ የተፈጠረው ከአስር ቀናት በፊት ሲሆን ሟቹ ማርያኖ እና ፍቅረኛው ናታሻ ፓልቫሲኖ እጅ ለእጅ ተያይዘው መንገድ ላይ እየተጓዙ በሚገኙበት ወቅት የቀድሞ የትምህርት ቤት ጓደኛውን መንገድ ላይ ያገኛል፡፡
ቀጥሎም ሁለቱ የቀድሞ የትምህርት ቤት ጓደኞች ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላ ስለሚገኙበት ሁኔታ እና ስለጤናቸው እየተጠያያቁ ባሉበት የሟቹ ፍቅረኛ ናታሻ በቦርሳዋ ይዛው የነበረውን ስለት አውጥታ ማሪዮን ሰላም ባለችው ሴት ላይ ጉዳት አድርሳለች፡፡
በአካባቢው የነበሩ ሰዎች በሀይለኛ ቁጣ ውስጥ ሆና ፍቅረኛዋን ሰላም ያለቸውን ሴት ህይወት ለማጥፋት ስትሞክር የነበረችውን ናታሻ ጣልቃ በመግባት ተጨማሪ ጉዳት ከማድረስ ቢያስጥሏትም የማሪዮን ህይወት ግን ሊታደጉ አልቻሉም፡፡
በስለት ከወጋቻት እንስት ላይ ተጨማሪ ጉዳት ከማድረስ በገላጋይ የተገለገለችው ናታሻ ቁጣዋን ወደ ፍቅረኛዋ አዙራ ደረቱ ላይ በስለት ወግታ ገድላዋለች፡፡
በማሪዮ ሴት ጓደኛ ደም የተነከረ ስለት ይዛ የተጠጋችው ናታሻ ግድያውን ከመፈጸሟ በፊት ለደቂቃዎች ከማሪዮ ጋር ከተጨቃጨቁ በኋላ በፍጥነት የሰነዘረችው ስለት ህይወቱ እንዲያልፍ ምክንያት ሆኗል፡፡
በአካባቢው የነበሩ ሰዎች ቀደም ሲል የተወጋችውን የማሪዮን የትምህርት ቤት ጓደኛ ሁኔታ መከታተል ላይ ትኩረት አድርገው ስለነበር የወጣቱን ህይወት ሊታደጉት አልቻሉም፡፡
የ32 አመቷ ናታሻ ከዚህ ቀደምም በአመጸኛ ባህሪዋ የምትታወቅ ሲሆን በ2021 የቀድሞ ፍቅረኛዋን በተመሳሳይ በስልት ወግታ የግድያ ሙከራ በማድረግ የአንድ አመት እስር ተፈርዶባት ነበር፡፡
ከዚህ ባለፈም ሟቹ ማሪያኖ ራሱ ናታሻን በግድያ ዛቻ እና አካላዊ ጥቃት ክስ ከፍቶባት እርሱ በሚገኝበት አካባቢ እንዳትገኝ የፖሊስ እግድ ወጥቶባት ነበር፡፡
ሆኖም በመካከላቸው ለሚገኝው የፍቅር ግንኙነት ሁለተኛ እድል ለመስጠት በመወሰኑ ጥንዶቹ ድጋሚ የፍቅር ግንኑነት ጀምረው ነበር፡፡