የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ከትራምፕ ጋር ለመምከር ዛሬ ወደ ዋሽንግተን ያቀናሉ
የኔታንያሁና ትራምፕ ምክክር በጋዛ የድህረ ጦርነት አስተዳደር፣ በእስራኤልና ሳኡዲ ግንኙነት ማደስ እና በኢራን ዙሪያ እንደሚያተኩር ተገልጿል
እስራኤልና ሃማስ በሁለተኛው ምዕራፍ የጋዛ ተኩስ አቁም ዙሪያ ከነገ ጀምሮ ድርድር ማድረግ እንደሚጀምሩ ይጠበቃል
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ዛሬ ወደ አሜሪካ ያቀናሉ።
ኔታንያሁ በዋሽንግተን ቆይታቸው ከፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር በሁለትዮሽና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ።
የኔታንያሁ እና ትራምፕ ምክክር በጋዛ የድህረ ጦርነት አስተዳደር፣ በእስራኤልና ሳኡዲ ግንኙነት ማደስ እና በኢራን ዙሪያ እንደሚያተኩር የእስራኤሉ ሃሬትዝ ጋዜጣ ምንጮቹን ጠቅሶ አስነብቧል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር በነገው እለት ከፕሬዝዳንት ትራምፕ የመካከለኛው ምስራቅ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ ጋር በሁለተኛው ምዕራፍ የጋዛ ተኩስ አቁም ዙሪያ ይመክራሉ።
ኔታንያሁ ለልዩ መልዕክተኛው በሁለተኛው ምዕራፍ ተኩስ አቁም ዙሪያ የእስራኤልን አቋም እንደሚገልጹ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
ይህ ምክክር እንደተጠናቀቀም ዊትኮፍ ከእስራኤልና ሃማስ አደራዳሪዎች (ኳታር እና ግብጽ) ባለስልጣናት ጋር እንደሚወያዩ ተገልጿል።
የእስራኤሉን ዋላ ኒውስ ዋቢ ያደረገው አናዶሉ ኔታንያሁ ከትራምፕ ጋር እስከሚመክሩ ድረስ ተደራዳሪዎቻቸውን ወደ ኳታር ላለመላክ መወሰናቸውን ዘግቧል።
በሁለተኛው ምዕራፍ የጋዛ ተኩስ አቁም እና የታጋቾችና እስረኞች ልውውጥ ዙሪያ ስምምነት ለመድረስ የሚካሄደው ድርድር በነገው እለት በኳታር ይጀመራል ቢባልም እስራኤል ግን ድርድሩ በዋሽንግተን እንደሚካሄድ አስታውቃለች።
ኔታንያሁ ከሞሳድ እና ሺን ቤት ሃላፊዎች እና ከፍተኛ ተደራዳሪዎች ጋር ሊያደርጉት የነበረውን ስብሰባ ሰርዘው ወደ ዶሃ የሚያቀኑበት ጊዜ መራዘሙን ማሳወቃቸውም ተዘግቧል።
የእስራኤል መንግስት ተደራዳሪዎች ነገ ወደ ዶሃ አያቀኑም በሚል ለወጣው ዘገባ እስካሁን ማስተባበያ አልሰጠም።
እስራኤልና ሃማስ በአሜሪካ፣ ኳታር እና ግብጽ አደራዳሪነት የደረሱት የተኩስ አቁም ስምምነት ከፈረንጆቹ ጥር 19 2025 ጀምሮ ተግባራዊ እየተደረገ ነው።
የተኩስ አቁም እና የታጋቾች ልውውጥ ስምምነቱ በሶስት ምዕራፍ የሚተገበር ሲሆን፥ ለ42 ቀናት የሚቆየው የመጀመሪያው ምዕራፍ ተፈጻሚ መሆን ከጀመረ ሁለት ሳምንት ተቆጥረዋል።
እስካሁን ሃማስ 13 እስራኤላውያን እና አምስት የታይላንድ ዜግነት ያላቸው ታጋቾችን የለቀቀ ሲሆን፥ እስራኤል 583 ፍልስጤማውያን እስረኞችን ፈታለች።
በመጀመሪያው ምዕራፍ 33 ታጋቾች ይለቀቃሉ ቢባልም የስምንቱ ህይወት ማለፉ የተነገረ በመሆኑ በቀጣይ ሳምንታት ቀሪዎቹ ሰባት ታጋቾች ይለቀቃሉ።
ከ70 በላይ ታጋቾች አሁንም በጋዛ የሚገኙ ሲሆን የታጋቾች እና እስረኞች ልውውጡ እንዳይቋረጥ እስራኤልና ሃማስ በሁለተኛው ምዕራፍ የጋዛ ተኩስ አቁም ስምምነት ዙሪያ በፍጥነት መግባባት ላይ መድረስ ይጠበቅባቸዋል