የፍልስጤም ፕሬዝዳንት መሀሙድ አባስ ከትራምፕ ጋር በቅርበት መስራት እንደሚፈልጉ ተናገሩ
ፕሬዝዳንቱ በፍልስጤም እና እስራኤል መካከል በሁለት ሀገርነት መፍትሔ ላይ መነጋገር እፈልጋለሁ ብለዋል
ዶናልድ ትራምፕ በመጀመሪያ የስልጣን ዘመናቸው የአሜሪካን ኢምባሲ ከቴልአቪቭ ወደ እየሩሳሌም እንዲዛወር ማድረጋቸው ይታወሳል
ፍልስጤሙ ፕሬዝዳንት መሀሙድ አባስ በዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆኖ መሾም የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት አስተላፈዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ በመልዕክታቸው በሁለት ሀገር መፍትሄ ላይ በመመስረት ከእስራኤል ጋር ሰላም ለመፍጠር ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
አባስ በዋፋ የዜና ወኪል ባወጡት መግለጫ "በእርስዎ የስልጣን ዘመን ሰላምን ለማስፈን ከአስተዳደረዎ ጋር ለመስራት ዝግጁ ነን" ብለዋል።
ይህ የሚሳካ ከሆነ የፍልስጤም እና የእስራኤል መንግስት በፀጥታ እና በሰላም ጎን ለጎን እየኖሩ በአከባቢያችው እንዲሁም በአለም ደህንነት እና መረጋጋት ላይ ሚና መጫዎት ይችላሉ ነው ያሉት፡፡
ዶናልድ ትራምፕ ከ2017 እስከ 2021 በነበራቸው የመጀመሪያ የስልጣን ዘመናቸው፤ የትራምፕ አስተዳደር እስራኤል የተቆጣጠረችውን ዌስት ባንክ ግዛቶች ባሉበት እንዲቆዩ እና በምላሹ ከምስራቅ እየሩሳሌም የተወሰነ አካባቢ ለፍልስጤም አሳልፋ የምትሰጥበትን የስምምነት ሀሳብ አቅርበው ነበር፡፡
በወቅቱ ፍልስጤማውን ሀሳቡን አጥብቀው የተቃወሙት ሲሆን እስራኤልም በአብርሀም አኮርድ ስምምነት ከአረብ ሀገራት ጋር ግንኙነቷን ማደስ ስትጀምር በዌስት ባንክ ስታደርግ የነበረውን የግዛት መስፋፋት አቁማ ነበር፡፡
ከዚህ ባለፈም ትራምፕ በእስራኤል የአሜሪካ ኢምባሲ ከቴልአቪቭ ተነስቶ ፍልስጤም ሀገር ሆና ስትመሰረት ዋና ከተማዋ እንደሆነች ወደሚነገርላት እየሩሳሌም እንዲዛወር መወሰናቸው ይታወሳል፡፡
የሁለት ሀገር መፍትሄ በእስራኤል እና ፍልስጤማውያን መካከል ላለፉት አስርት አመታት የሰላም ድርድር መሰረት ሆኖ የቆየ ቢሆንም የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ነጻ የሆነች ፍልስጤም በሀገርነት መመስረትን ደጋግመው ሲቃወሙ ተስተውለዋል።
አባስ የሚመሩት በራማላ ላይ የሚገኘው የፍልስጤም አስተዳደር ከጦርነቱ በኋላ በጋዛ ሰርጥ ላይ ምንም አይነት ሚና እንዳይኖረውም አሳስበዋል፡፡
በዋሽንግተን ቴልአቪቭ ግንኙነት ምርጡ የእስራኤል አጋር በመባል የሚጠሩት ትራምፕ ስትራቴጂያዊ አሰላለፍ ለውጥ በታየበት መካከለኛው ምስራቅ እስራኤል እና ፍልስጤምን በተመለከተ የሚከተሉት ፖሊሲ ወሳኝነቱ የጎላ ነው።