ኔታንያሁ የጋዛው ጦርነት እንዲቀጥል ከአጋራቸው ድጋፍ ለማግኘት ወደ አሜሪካ አቀኑ
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር የፊታችን ረቡዕ በአሜሪካ ኮንግረንስ ንግግር ያደርጋሉ
እስራኤል በጋዛ የምትፈጽመውን ድብደባ የሚቃወሙ አካላት በዋሽንግተን ግዙፍ የተቃውሞ ሰልፍ ጠርተዋል
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ወደ አሜሪካ አቀኑ።
በጋዛው ጦርነት ምክንያት በሀገር ውስጥም ሆነ በአለማቀፍ ደረጃ ጫናው የበረታባቸው ኔታንያሁ ይህን ጉብኝት ከአጋራቸው አሜሪካ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለማለዘብ ይጠቀሙበታል ተብሏል።
ኔታንያሁ በ2022 ለሁለተኛ የስልጣን ዘመን ከተመረጡ በኋላ በአሜሪካ የመጀመሪያውን ጉብኝታቸውን ለማድረግ ጉዞ የጀመሩት ዴሞክራቱ ጆ ባይደን ከህዳሩ ወር ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ራሳቸውን ማግለላቸውን ባሳወቁ ማግስት ነው።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር በኮቪድ 19 የተጠቁት ጆ ባይደን በፍጥነት የሚያገግሙ ከሆነ በነገው እለት ምክክር ያደርጋሉ ተብሏል።
ከነገ በስቲያ ረቡዕም ከዘጠኝ አመት በኋላ በአሜሪካ ኮንግረንስ በመገኘት ንግግር እንደሚያደርጉ ነው ሬውተርስ የዘገበው።
በጋዛው ጦርነት ምክንያት ከዋነኛ አጋራቸው ዋሽንግተን ጋር ግንኙነታቸው የሻከረው ኔታንያሁ በካፒቶል ሂል ከዘጠኝ አመት በፊት ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማን (ከኢራን ጋር የኒዩክሌር ስምምነት በመፈራረማቸው) እንደተቹበት አይነት ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ አይጠበቅም።
ዴሞክራቶች ለእስራኤል በቂ ድጋፍ አልሰጡም ባሉ ሪፐብሊካኖች ተጋብዘው በኮንግረንሱ ንግግር የሚያደርጉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የጋዛው ጦርነት ወደ ሌሎች የመካከለኛ ምስራቅ ሀገራት አድማሱን እያሰፋ እንደሚሄድ በስፋት ያነሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ዘጠኝ ወራት ያስቆጠረው ጦርነት ካልቆመ ለእስራኤል የጦር መሳሪያ ድጋፍ አቋርጣለሁ የምትለው ዋሽንግተን ከማስፈራሪያ ያለፈ ጠንከር ያለ እርምጃ ባትወስድም በቀጣዩ ምርጫ ለዴሞክራቶች የደቀነው ስጋት ተደጋጋሚ መግለጫዎችን እንድታወጣ አድርጓት ነበር።
ኔታንያሁ በአሜሪካ ቆይታቸው ከሪፐብሊካኑ ፕሬዝዳንታዊ እጩ ዶናልድ ትራምፕ ጋር ለመገናኘት ቀጠሮ ስለመያዛቸው እስካሁን የተባለ ነገር የለም።
ትራምፕ በስልጣን ዘመናቸው ከኔታንያሁ ጋር ጥብቅ ወዳጅነት መስርተው ለእስራኤል የወገኑ ውሳኔዎችን ቢያሳልፉም የአሁኑ የጋዛው ጦርነት ግን በፍጥነት እንዲቆም በማሳሰብ ኔታንያሁን መተቸታቸው ይታወሳል።
በእስራኤልም ሆነ አጋሯን አሜሪካ ጨምሮ በአለማቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ የጋዛውን ጦርነት ያቆሙ ዘንድ ጫናው ያየለባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ፥ የአሜሪካ ጉብኝታቸው ተቃውሞ እንደሚበዛበት ይጠበቃል።
ኔታንያሁ ለ39 ሺህ ፍልስጤማውያን ህልፈት ተጠያቂ ናቸው ያሉ ተቃዋሚዎች በካፒቶል አዳራሽ ዙሪያ ግዙፍ የተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ ቅስቀሳ ጀምረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጥቅምት 7ቱ የሃማስ ጥቃት ታግታ ተወስዳ የነበረችውንና ባለፈው ወር በእስራኤል ኮማንዶ ነጻ የወጣችውን ናኦ አርጋማኒ ይዘው ነው ወደ አሜሪካ የሚያቀኑት።
ይህም በሀገር ቤት ለዘጠኝ ወራት ይኑሩ ይሞቱ የማይታወቁ 120 ዜጎችን ማስለቀቅ አልቻሉም በሚሉ የታጋች ቤተሰቦች ተቃውሞ እየተነሳበት ነው።