እስራኤል በማዕከላዊ ጋዛ በፈጸመችው ከባድ ጥቃት በርካቶች ተገደሉ
እስራኤል ባለፉት ሳምንታት እያካሄደች ባለው የተጠናከረ የአየር እና የታንክ ጥቃቶች በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል
እስራኤል ጥቃቶቹ በደህንነት መረጃዎች ላይ የተመሰረቱ እና ታጣቂዎችን ኢላማ ያደረጉ ናቸው ብላለች
እስራኤል በማዕከላዊ ጋዛ በፈጸመችው ከባድ ጥቃት በርካቶች ተገደሉ።
የእስራኤል ጦር በትናንትናው እለት በማዕከላዊ ጋዛ ባደረሰው ጥቃት በአል ኑሰሪያት ከምፕ አቅራቢያ ቢያንስ ስምንት ሰዎች የተገደሉ ሲሆን በደቡባዊቷ የራፋ ከተማ እየተካሄደ ባለው ከባድ ጦርነት ደግሞ አምስት ነዋሪዎች መገደላቸው ተገልጿል።
እስራኤል ባለፉት ሳምንታት እያካሄደች ባለው የተጠናከረ የአየር እና የታንክ ጥቃቶች በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል።
የፍልስጤም የጤና ባለስልጣናት እንደሚሉት ከሆነ በአል-ኑሰሪያት አርብ ጠዋት በሁለት ቤቶች ላይ በተፈጸሙ ሁለት የተለያዩ ጥቃቶች ስምንት ሰዎች ተገደልዋል።
እስራኤል የሀማስ የመጨረሻ የሀማስ ምሽግ ይገኝባታል በምትላት የራፋ ከተማ ከፍተኛ ጦርነት እየተካሄደ መሆኑን ሮይተርስ የአይን እማኞችን ጠቅሶ ዘግቧል።
የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች በእስራኤል ተኩስ አምስት ሰዎች መገደላቸውን እና አስከሬናቸውም በካን ዮኒስ ወደሚገኘው ናሰር ሆስፒታል መወሰዱን ተናግረዋል። እስራኤል ተፈናቃዮች የሰብአዊ ቀጠና ሆኗል ወደተባለው አል ማዋሲ እንዲሄዱ ብታሳስብም፣ ቦታው እስራኤል በምታደርሰው ተደጋጋሚ የአየር ድብደባ አስጊ እንደሆነባቸው ነዋሪዎች እየተናገሩ ናቸው።
"አል-ማዋሲ ሰላማዊ ቦታ ነው አሉን... ወደ ሰላማዊ ቦታ መጣን፣ የምን ሰላም? ጋዛ ውስጥ ሰላማዊ ቦታ የለም። ካን ዮኒስ ወደሚገኘው አል-ማዋሲ እንድንሄድ የነገሩን እነሱ ናቸው። ባሉት መሰረት መጣን፣ ካምፕ ውስጥ መቱን፤ ድንኳኑ ውስጥ ግባና እየው ፍንጥርጣሪ ብቻ ነው"ሲሉ ባሏ የተገደለባት አዚዝ ሱሌማን አማር የተባለች ፍልስጤማዊ ሴት ተናግራለች።
አማር እንደገለጸችው "መሄጃ የለንም። ቤታችን ወድሟል። ቤት የለኝም፤ ባለቤቴም ሞቷል። ቀጥሎ ምን እንደሚፈጠር ፈጣሪ ነው የሚያውቀው።"
እስራኤል ጥቃቶቹ በደህንነት መረጃዎች ላይ የተመሰረቱ እና ታጣቂዎችን ኢላማ ያደረጉ መሆናቸውን ብትገልጽም፣ ፍልስጤማውያን ግን ሀሰት ነው ይላሉ።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ በራፋ ባደረጉት ድንገተኛ ጉብኝት ወታደራዊ ጫናው 120 ታጋቾችን ለማስለቀቅ በሚደረገው ጥረት ውጤት እያመጣ ነው ብለዋል።
በግብጽ፣ ኳታር እና አሜሪካ የተጀመረው የእስራኤል-ሀማስ ተኩስ የማቆም ድርድር እስካሁን ውጤት አላመጣም።
እስራኤል፣ ባለፈው ጥቅምት ወር ድንበር ጥሶ ከባድ ጥቃት ባደረሰባት ሀማስ ላይ እየወሰደች ባለው ጥቃት ሳቢያ የተገደሉ ፍልስጤማውያን ቁጥር ከ38ሺ ማለፉን የጋዛ የጤና ባለስልጣን መረጃ ያመለክታል።