ኔታንያሁ እስራኤል እየጨመረ ለመጣው አለማቀፍ ጫና ሸብረክ እንደማትል ተናገሩ
ልኡካቸው በዋሽንግተን ሊያደርገው የነበረው ጉዞ የተሰረዘውም የጋዛውን ጦርነት የሚያስቆመው እንደሌለ ለሃማስ መልዕክት ለማስተላለፍ ነው ብለዋል
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሜሪካ በጸጥታው ምክርቤት ያሳየችውንን የአቋም ለውጥም ተቃውመዋል
እስራኤል በጋዛ የጀመረችውን ሃማስን የመደምሰስ ጦርነት የሚያስቆማት ሃይል የለም አሉ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ።
አለማቀፍ ጫናው እየበረታ ቢመጣም እስራኤል ላይ የሚፈጥረው አንዳች ተጽዕኖ እንደሌለው ነው ጠቅላይ ሚንስትሩ የተናገሩት።
ኔታንያሁ ከአሜሪካው ሴናተር ሪክ ስኮት ጋር ያደረጉትን ምክክር ተከትሎ በተቀዳ የቪዲዮ ምስል ለአሜሪካ እና ሃማስ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ዋሽንግተን ባለፈው ሰኞ በጋዛ ተኩስ እንዲቆም በቀረበው የጸጥታው ምክርቤት ውሳኔ ሃሳብ ላይ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብቷን ተጠቅማ ተቃውሞዋን ከማሰማት ይልቅ ተአቅቦን መምረጧ ይታወሳል።
ከሶስት ጊዜ በላይ በጋዛ በአስቸኳይ ጦርነት እንዲቆም የቀረቡ የውሳኔ ሃሳቦችን ውድቅ ያደረገችው አሜሪካ ድምጸ ተአቅቦን መምረጧ በጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ “በጣም መጥፎ የአቋም ለውጥ” ተብሎ ተተችቷል።
የጸጥታው ምክርቤት ያሳለፈው ውሳኔ ለሃማስ የተሳሳተ መልዕክት መስደዱንም ጠቅሰዋል።
“የውሳኔው መጥፎ ነገር ሃማስ አለማቀፉ ጫና እስራኤል ታጋቾችን ለማስለቀቅና ቡድኑን ለመደምሰስ የጀመረችውን ጦርነት ያስቆማል የሚል ጠንካራ አቋም እንዲይዝ አድርጓል” ሲሉም ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ “ሃማስ አለማቀፍ ጫናዎች እስራኤል ላይ እንደማይሰሩ ሊረዳ ይገባል” ያሉት ኔታንያሁ፥ የእሳኤል ልኡክ በአሜሪካ ሊያደርገው የነበረው ጉብኝት የተሰረዘውም ለቡድኑ መልዕክት ለማስተላለፍ ነው ብለዋል።
እስራኤል ለአለማቀፍ ጫና ትንበረከካለች ብሎ ማሰብ የዋህነት መሆኑን በማንሳትም የጋዛው ጦርነት ቀጣይነቱን አረጋግጠዋል ያላል የሬውተርስ ዘገባ።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተያየት አለማቀፉን ተቋም የመንግስታቱ ድርጅት ዝቅ ያደረገ ነው የሚሉ ተንታኞች፥ የቴል አቪቭ ዋነኛ አጋር አሜሪካ በቀጣይ የምታሳልፈው ውሳኔ ተጠባቂ መሆኑን ያነሳሉ።
ዋሽንግተን ከሰባት አስርት በላይ ወዳጇ ቴል አቪቭ ላይ የሚጨክን አንጀት እንደሌላት ግን ያምናሉ።
የመንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብት ባለሙያ ፍራንሴስካ አልባኔዝ በጄኔቫ በጋዛ የዘር ማጥፋት ፈጽማለች የሚል ሪፖርታቸውን ሲያቀርቡ ሀገራት በእስራኤል ላይ የጦር መሳሪያ ማዕቀብ እንዲጥሉ ጠይቀዋል።
የእስራኤሉ የመከላከያ ሚኒስትር ዮቭ ጋላንት በበኩላቸው የጦር መሳሪያ ድጋፍ ለማግኘት ዋሽንግተን ከገቡ ቀናት ተቆጥረዋል።
ኔታንያሁ ከዶሃ ተደራዳሪዎችን እንዲወጡ በማዘዝ ከ32 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያንን ህይወት የቀጠፈውን ጦርነት የሚያስቆም አንዳች ሀይል የለም ማለታቸውም ዋሽንግተን የጦር መሳሪያ ድጋፍ ሳታደርግ አልቀረችም የሚለውን ጥርጣሬ አጉልቶታል።