ኔታንያሁ የእስራኤልን የልኡካን ቡድን የዋሽንግተን ጉዞ እቅድ መሰረዛቸው አሜሪካን አስቆጣ
ክርቢይ አሜሪካ በተመድ ድምጸ ተአቅቦ ብታደርግም የአሜሪካ ፖሊሲ አልተቀየረም ብለዋል
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከፍተኛ የእስራኤል የልኡካን ቡድን በዋሽንግተን ሊያደርገው የነበረውን የጉዞ እቅድ ሰርዘዋል
ኔታንያሁ የእስራኤልን የልኡካን ቡድን የዋሽንግተን ጉዞ እቅድ መሰረዛቸው አሜሪካን አስቆጣ።
አሜሪካ በተመድ በቀረበው የተኩስ አቁም የውሳኔ ሀሳብ ላይ ድምጽ ተአቅቦ ካደረገች በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከፍተኛ የእስራኤል የልኡካን ቡድን በዋሽንግተን ሊያደርገው የነበረውን የጉዞ እቅድ ሰርዘዋል።
አሜሪካ በእሰራኤል ድርጊት ከፍተኛ ብስጭት እንደተሰማት ገልጸለች።
"ይህ በጣም የሚያበሳጭ ነው። በራፋ ሰላለው ሁኔታ አማራጮችን ለመፈለግ የሚያስችል ውይይት እንድናካሂድ የሚያስችለንን የዋሽንግተን ጉዞ በመሰረዛቸው በጣም ተበሳጭተናል"ብለዋል የኃይትሀውስ ቃል አቀባይ ጆን ክርቢይ።
ክርቢይ እንደተናገሩት ከፍተኛ የአሜሪካ ባለስልጣናት ለስራ ጉብኝት አሜሪካ ከሚገኙት የእስራኤሉ የመከላከያ ሚኒስትር ዩአቭ ጋላንት ጋር በታጋቾች፣ በሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት እና በራፋ ለንጹሃን ሊደረግ ስለሚገባው ከለላ ጉዳይ ተገናኝተው ይወያያሉ።
ክርቢይ አሜሪካ በተመድ ድምጸ ተአቅቦ ብታደርግም የአሜሪካ ፖሊሲ አልተቀየረም ብለዋል።
የአሜሪካ ባለስልጣናት እስራኤል በጋዛ ጉዳይ በምታራምደው ፖሊሲ ዙሪያ ያላቸውን ስጋት ማንሳታቸውን ይቀጥላሉ ሲሉ ክርቢይ ተናግረዋል።
ክርቢይ "በራፋ ሊደረግ የሚችል የእግረኛ ጦር ጥቃት ትልቅ ስህተት ነው የሚለውን እይታችንን የሚቀይረው ምንም ነገር የለም" ብለዋል።
እሰራኤል በጋዛ ድንበር የምትገኘዋን እና ጦርነት ሸሽተው የተፈናቀሉ ሰዎች የተጠለሉባትን በግብጽ ድንበር የምትገኘውን የራፋ ከተማን ለማጥቃት የያዘችውን እቅድ በቅርቡ ማጽደቋ ይታወሳል።
ግብጽን ጨምሮ እስራኤልን እና ሀማስን እያደራደሩ ያሉ አካላት ይህን የእስራኤልን እቅድ የከፋ አደጋ ያስከትላል በሚል ተቃውመውታል።