በእስራኤልና ፍሊስጤም መካከል አዲስ ስለተቀሰቀሰው ጦርነት እስካሁን የምናውቀው…
የእስራኤል ጠ/ሚ ኔታንያሁ “እኛ ጦርነት ላይ ነን” ሲሉ ለሀገሪቱ ዜጎች መልእክት አስተላልፈዋል
በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት የከፈተው ሃማስ "ለመጨረሻ ጊዜ በቃን ብለን ተነስተናል" ብሏል
በእስራኤል እና ፍልስጤም መካከል በጋዛ ሰርጥ አካባቢ ሃማስ የከፈተውን ድንገተኛ ጥቃት ተከትሎ በዛሬው እለት አዲስ ጦርነት መቀስቀሱ ተነግሯል።
ሃማስ በጋዛ ሰርጥ በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎ በርካታ የሃማስ ታጣቂ ቡድን አባላት ታጣቂዎች ወደ ደቡብ እስራኤል ገብተዋል።
የሃማስ መሪ መሀመድ ዴፍ እንዳሉት በሺዎች የሚቆጠሩ ሮኬቶች ከጋዛ ወደ እስራኤል ተተኩሰዋል። በ20 ደቂቃ ውስጥ 5 ሺ ሮኬት መተኮሳችውንም ቢቢሲ ዘግቧል።
የሀማስ መሪ መሐመድ ዴፍ "ለመጨረሻ ጊዜ በቃን ብለን ተነስተናል" ሲል ተናግሯል።
እስራኤል የፍልስጤም ታጣቂ ቡድን ሃማስ በጋዛ ሰርጥ በኩል በፈፀመው ጥቃት ህይወታቸው ያለፈ እስራዔላውያን ቁጥር 40 መድረሱን እና የቆሰሉ ሰዎች ቁጥር ደግሞ 740 መድረሱን አረጋግጣለች።
የእስራዔል መከላከያ ሚኒስቴር “በርካታ አሸባሪዎች” የእስራኤልን ግዛት ከጋዛ ሰርገው ገብተዋል ብሏል።
የእስራኤል የደህንነት ካቢኔ አስቸኳ ስብሰባ የተጠራ ሲሆን፤ የእስራዔል መከላከያ ሰራዊት በሃማስ ኢላማዎች ላይ ጥቃት መሰንዘር መጀመሩ ተነግሯል።
የእስራዔል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በቪዲዮ ማስተላለፉት መግለጫ፤ “እኛ ጦርነት ላይ ነን” ተናግረዋል።
ጦራቸው እንዲንቀሳቀስ ያዘዙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ፤ “ጠላት የማያውቀው ጥንካሬ እና ስፋት ያለው የአጸፋ ጦርነት አዝዣለሁ” ብለዋል።
“ጠላት ከዚህ ቀደም አይቶት የማያውቀውን ዋጋ ይከፍላል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ፤ እስከዚያው ግን ሁሉም የእስራኤል ዜጎች የሠራዊቱን መመሪያ እና የአገር ውስጥ ዕዝ መመሪያዎችን በጥብቅ እንዲከታተሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የእስራኤል መከላከያ ሚንስትር ዮአቭ ጋላንት ሃማስ “ከባድ ስህተት ሰርቷል” ሲሉ “የእስራኤል መንግስት በዚህ ጦርነት እንደሚያሸንፍ አስታውቀዋል።
የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ፤ እስራዔል ራሷን የመከላከል ሙሉ መብት አላት ያሉ ሲሆን፤ ጀርመን እና ጣሊያን በእስራኤል ላይ የተፈፀመውን ጥቃት አውግዘዋል።
በእስራዔል ላይ የተቃጣውን ጥቃት ያወገዘችው አሜሪካም፤ ለእስራዔለ ሙሉ ድጋፍ እንደምታደርግ አስታውቃለች።
በደቡባዊ እስራኤል በተለያዩ ቦታዎች በእስራኤል እና በፍልስጤም ጦር መካከል የተኩስ ፍልሚያ አሁንም መቀጠሉን የእስራኤል መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።