እስራኤልና ፍልስጤም ከ30 አመት በፊት የተፈራረሙት የኦስሎ ስምምነት ምን ይላል?
ይስሃቅ ራቢን እና ያሲር ራፋት በዋይትሃውስ የፈረሙት ስምምነት ብዙ ተስፋ ቢጣልበትም ግጭት ማብረድ አልቻለም
ስምምነቱ የወቅቱን ፈራሚዎች የኖቬል የሰላም ሽልማት አሸልሟል፤ ለይስሃቅ ራቢን ግድያም ምክንያት ሆኗል
ከሶስት አስርት አመታት በፊት በኖርዌይ ድርድር ሲደረግ ቆይቶ በዋሽንግተን የተፈረመው የኦስሎ ስምምነት የእስራኤልና ፍልስጤምን ግጭት ያስቆማል የሚል ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶት ነበር።
በወቅቱ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ይስሃቅ ራቢን እና የፍልስጤም የነጻነት ድርጅት (ፒኤልኦ) መሪው ያሲር አራፋት እጃቸውን መጨባበጣቸውም ከያኔው የእስራኤልየውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሺሞን ፔሬዝ ጋር የኖቬል የሰላም ሽልማት እንዲሰጣቸው አድርጓል።
አሁን ሶስቱም የኖቬል ተሸላሚዎች በህይወት የሉም፤ ይስሃቅ ራቢን ከስምምነቱ ጋር በተያያዘ መገደላቸውም ይታወሳል።
እስራኤል እና ፍልስጤም ወደ ሰላም ንግግር እንዲመለሱ በር የከፈተው ስምምነት ከራቢን እና አራፋት እጅ መጨባበጥ ውጭ ያመጣው ለውጥ ያለ አይመስልም።
ታሪካዊው የኦስሎ ስምምነት ምን ይላል?
የመጀመሪያው የኦስሎ ስምምነት (ኦስሎ 1) በፈረንጆቹ መስከረም 18 1993 በዋይትሃውስ ተፈርሟል።
በዚህ ስምምነት እስራኤልና ፍልስጤም ለመጀመሪያ ጊዜ እውቅና የተሰጣጡበትና የአስርት አመታቱን ግጭት ለማቆም መስማማታቸው አይዘነጋም።
ሁለተኛው ስምምነት (ኦስሎ 2) በመስከረም ወር 1995 ሲፈረም የሰላም ስምምነት የሚፈረምበትን ሂደት በተመለከቱ ዝርዝር ጉዳዮች መግባባት ላይ ተደርሶ ነበር።
ፍልስጤማውያን የተወሰደባቸው መሬት ይመለስላቸዋል፤ እንደ ሀገርም እውቅና ያገኛሉ የሚለው ስምምነት ሂደቱን በተመለከተም በዝርዝር ምክክር ተደርጎ እንደሚወሰን ያስቀምጣል።
ስምምነቱን ወደ ተግባር ለመለወጥ የእስራኤል ወታደሮች በ1967ቱ የስድስት ቀናት ጦርነት በሃይል ከተያዙ የፍልስጤም ይዞታዎች ይልቀቁ፤ ስልጣን ወደ ፍልስጤም አስተዳደር ይተላለፍ የሚሉና ሌሎች ጉዳዮች መፈጸም ነበረባቸው።
የምስራቃዊ እየሩሳሌም ከተማ ጉዳይ እና የእስራኤል ሰፈራ ፕሮግራም በይደር ቆይተው ይመከርባቸዋል የሚለው የኦስሎ ስምምነት ጊዜያዊ የፍልስጤም አስተዳደር ተቋቁሞ የሚያስተዳድራቸው አካባቢዎች እንዲለዩም ያስቀምጣል።
ከኦስሎው ስምምነት በኋላ ባሉት አምስት አመታት ውስጥ የመጨረሻ ስምምነት ይደረሳል ቢባልም እስካሁን እውን ሊሆን አልቻለም።
የኦስሎው ስምምነት ከማን ተቃውሞ ገጠመው?
የእስራኤል ቀኝ ዘመም ፖለቲከኞች እንደ “ሽብርተኛ ድርጅት” ከሚመለከቱት የፍልስጤም ነጻ አውጪ ድርጅት (ፒኤልኦ) ጋር የሚደረግ ንግግርንም ሆነ ስምምነት በፍጹም እንደማይቀበሉት በተደጋጋሚ ሲገልጹ ይደመጣል።
በሰፈራ ፕሮግራም በፍልስጤም የሚኖሩ እስራኤላውያንም ስምምነቱ ከመኖሪያችን ሊያፈናቅለን ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው ይነገራል።
የኦስሎ ስምምነትን ከያሲን አራፋት ጋር የፈረሙት ይስሃቅ ራቢን በ1995 ይህንኑ ስምምነት በተቃወመ እስራኤላዊ ወታደር በአደባባይ መገደላቸውም የሚታወስ ነው።
በፍልስጤም ወገንም እንደ ሃማስ ያሉ ቡድኖች የኦስሎው ስምምነት ፍልስጤማውያን በ1948 ወደተነጠቁት ርስታቸው እንዲመለሱ የማያደርግ ነው በሚል ሲቃወሙት እንደነበር በታሪክ ተሰንዷል።
የፍልስጤም ነጻነት ድርጅት (ፒኤልኦ) መሪ የነበሩት ያሲር አራፋትም በሽብርተኝነት ስሙ ሲነሳ የቆየውን ሃማስ እያወደሱ በእስራኤል ላይ የሽብር ጥቃቶች እንዲፈጸሙ ማድረጋቸው ይነገራል።
ይስሃቅ ራቢንን የተኩት የእስራኤል መሪዎችም (ቤንያሚን ኔታንያሁ እና ኤሪያል ሻሮን) አስቀድመው የኦስሎውን ስምምነት ሲቃወሙ እንደመቆየታቸው ስምምነቱን ቀደው መጣላቸው የሚጠበቅ ነው።
እናም በኦስሎው ስምምነት መሰረት እስራኤል ወታደሮቿን ከዌስትባንክ እንድታስወጣ ከማድረግ ይልቅ የሰፈራ ፕሮግራሙን ማስቀጠልና በፍልስጤም አስተዳደር ስር ባሉ አካባቢዎች የአየር ጥቃቶችን መፈጸም ላይ ትኩረት አድርገዋል።
በ1967ቱ የስድስት ቀናት ጦርነት ዌስትባንክ፣ ጋዛ ሰርጥ እና እየሩሳሌም በእስራኤል በሃይል ተይዞብናል የሚሉት ፍልስጤማውያን ስምምነቱ ለእስራኤል የሰፈራ ፕሮግራም ህጋዊ እውቅና ከመስጠት ውጭ ፋይዳ እንደሌለው ያምናሉ።
ከ30 አመት በፊት መግባባት የተደረሰበት ስምምነት ተፈጻሚ ሳይሆን በመቅረቱ የእስራኤልና ፍልስጤም ውጥረት የየእለቱ የአለማቀፍ መገናኛ ብዙሃን ትኩረት ሆኖ እንደቀጠለ ነው።